የማራቶን ክብረ ወሰንን በመስበር በጊነስ የድንቃ ድንቅ መዝገብም ላይ ስሟን እያስመዘገበችው ኢትዮጵያዊት አትሌት
አትሌት ትዕግሥት አሰፋ ተወልዳ ያደገችው ከአዲስ አበባ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች በምትርቀው ሆለታ ነው። ስድስት ልጆችን ለታደለው ቤተሰብ እርሷ የመጨረሻ ልጅ ናት። ሆለታ ውስጥ አራዳ ምሥራቅ ሜዳ በሚባል ትምህርት ቤት የተማረችው ትዕግሥት፣ በትምህርት ቤት በሚደረግ ውድድር ነበር ወደ አትሌቲክሱ የገባችው።
በሩጫው 400 ሜትር፣ 800 ሜትር እንዲሁም ግማሽ ማራቶን ሮጣለች። አገሯን በአፍሪካ ሻምፒዮና፣ በኦሊምፒክ ወክላለች። አሁን ደግሞ ትዕግሥት በአስደናቂ የሰዓት ልዩነት የሴቶች ማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤት ሆናለች። አትሌት ትዕግሥት አስደናቂው ድሏ እና ተያያዥ ጉዳዮች ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርጋለች።በሴቶች ማራቶን ውድድር ላይ ከፍተኛውን የሰዓት ቅናሽ በማምጣት ባለፈው ዓመት ክብረወሰን የሰበረችው ትዕግሥት አሰፋ በኦሊምፒክ መድረክ የብር መዳሊያ በታላቁ የለንደን ማራቶን አሸናፊ በመሆን ክብረ ወሰን አስመዝግባላች። በጊነስ የድንቃ ድንቅ መዝገብም ላይ ስሟ ተመዝግቧል፡፡ ኢትዮጵያዊቷ ትዕግሥት በለንደን ማራቶን አሸናፊ በመሆን ድል የተቀዳጀችው ሴቶች ብቻ በተሳተፉበት የማራቶን ውድድርን ክብረወሰንን ለግማሽ ደቂቃ በቀረበ ጊዜ ለማሻሻል ችላለች።

ባለፈው ዓመት በተካሄደው የፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ ከኔዘርላንዳዊቷ ሲፋን ሐሰን ጋር እስከ መጨረሻው ድረስ ተፎካክራ ትዕግሥት ሁለተኛ በመሆን የኦሊምፒክ ብር ሜዳሊያ አሸናፊ መሆኗ ይታወሳል።
ትዕግሥት አሰፋ በለንደን ማራቶን አሸናፊ የሆነችው ውድድሩን ከአራት ዓመት በፊት ያሸነፈችውን ኬንያዊቷን ጆይስሊን ጄፕኮስጌይን አስር ኪሎሜትር እየቀራት በሰፊ ልዩነት ርቃት በመሄድ ነው። ውድድሩን ስታጠናቅቅም ሁለት ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ50 ሰከንድ የሆነ ጊዜን አስመዝግባለች።
በትዕግሥት አሰፋ የተቀደሙት ኬንያዊቷ ጄፕኮስጌይን ሦስት ደቂቃ ከሚጠጋ ጊዜ በኋላ ሁለተኛ ስትወጣ፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ኔዘርላንዳዊቷ ሲፋን ሐሰን ደግሞ ሦስተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቃለች።
አሁን ትዕግሥት ያስመዘገበችው ሰዓት ባለፈው ዓመት በተደረገው የለንደን ማራቶን በኬንያዊቷ ፔሬዝ ጄፕቺርቺር ተይዞ የነበረውን የውድድሩን ክብረ ወሰን በ26 ሰከንዶች ለማሻሻል አስችሏታል።ትዕግሥት አሰፋ ባለፈው ዓመት መስከረም 13/2016 ዓ.ም. በጀርመን በርሊን በተካሄደው 48ኛው የበርሊን ማራቶን ውድድር የዓለም ክብረ ወሰንን ከሁለት ደቂቃ በላይ በማሻሻል 2 ሰዓት ከ11 ደቂቃ ከ53 ሰከንድ መግባቷ ይታወሳል።
ውዝግብ ተሰምቶበት ከነበረው የፓሪስ ኦሊምፒክ የማራቶን ውድድር በኋላ የዓለማችን ሴት የማራቶን ኃያላን የሆኑት ትዕግሥት አሰፋ እና ሲፋን ሐሰን የተሳተፉበት ይህ የዘንድሮው የለንደን ማራቶን ከባድ ፉክክር የሚደረግበት ነው ተብሎ ተጠብቆ ነበር። በፓሪስ ኦሊምፒክ የማራቶን ውድድር ላይ ትዕግሥት እና ሲፋን እስከ መጨረሻው ሰዓት ድረስ እግር በእግር እየተከታተሉ በመሮጥ አስደናቂ ፉክክር ያደረጉ ሲሆን፣ በመጨረሻ ላይ ሁለቱ አትሌቶች መካከል በተፈጠረው አካላዊ ንክኪ ምክንያት ትዕግስት በሲፋን ተገፍታ ሚዛኗን በመሳቷ ሲፈን አሸናፊ ሆናለች የሚል ውዝግብ ተነስቶ ነበር።
ቢሆንም ግን ቅሬታው ተቀባይነት ሳያገኝ ሲፋን የፓሪስ ኦሊምፒክ የማራቶን ውድድር አሸናፊ በመሆን ክብሩን ወስዳለች። ትዕግሥትም የብር ሜዳሊያ ባለቤት ለመሆን በቅታለች። ይህ ክስተትም ሁለቱ አትሌቶች በቀጣይ በሚኖሩ ውድድሮች ላይ የበላይ በመሆን የፓሪስ ኦሊምፒክ ውዝግብን መቋጫ ይሰጣሉ ተብሎ ሲጠበቅ ቆይቷል።
ስለዚህም የለንደን ማራቶን ውድድር በአዘጋጆቹ እና በአትሌትክስ አፍቃሪያን ዘንድ በሁለቱ እንስት ስፖርተኞች መካከል ከፋተኛ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ተጠብቆ ነበር። ትዕግሥት እና ሲፋን በውድድሩ ጅማሬ ላይ ከፊት ከሚመሩት ሯጮች መካከል በመሆን እስከ ውድድሩ አጋማሽ ርቀት ድረስ አብረው ቆይተዋል። 20 ኪሎ ሜትር ከተገባደደ በኋላ ግን ሲፈን ከትዕግሥት አምስት ሰከንድ ወደ ኋላ ስትቀር፣ ጄፕኮስጌይ ግን በቅርብ ርቀት ትዕግስትን በመከተል ለመፎካከር ሞክራለች።
እስከ 35ኛው ኪሎ ሜትር ድረስ ትዕግሥት እና ጄፕኮስጌይ ሳይነጣጠሉ ከሮጡ በኋላ ትዕግሥት ፍጥነቷን በመጨመር በመካከላቸው ያለውን ክፍተት በማስፋት ከኬንያዊቷ ተፎካካሪዋ ጋር ያላትን ትንቅንቅ አለዘበችው።በዚህም ትዕግሥት የውድድሩ 40ኛ ኪሎ ሜትር ላይ ስትደርስ በመካከላቸው የነበረው የሰዓት ልዩነት ወደ 56 ሰከንድ ሰፍቶ ነበር። በመጨረሻም ትዕግሥት አሰፋ ፓሪስ ላይ ሁለተኛ ሆና ያጣችውን አሸናፊነት ለንደን ላይ በማካካስ በ2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ50 ሰከንድ በመግባት ክብረ ወሰን በማሻሻል ድል አድርጋለች።
ሁለተኛ ደረጃ ላይ ኬንያዊቷ ጆይስሊን ጄፕኮስጌይን በ2 ሰዓት ከ18 ደቂቃ ከ43 ሰከንድ፣ ኔዘርላናዳዊቷ ሲፋን ሐሰን ደግሞ በ2 ሰዓት ከ18 ደቂቃ ከ59 ሰከንድ ሦስተኛ ሆናለች። ትዕግሥት ከድሏ በኋላ “ባለፈው ዓመት በውድድሩ ሁለተኛ ነበር የወጣሁት፤ በዚህ ዓመት ደግሞ አሸነፍኩ ይህ ልዩ ነው። በጣም ደስ ብሎኛል” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
“ባለፈው ዓመት በነበረው ቅዝቃዜ ችግር ነበረብኝ፣ በውድድሩ መጨረሻ ላይ ታፋዬ ላይ ህመም አጋጥሞኝ ነበር። በዚህ ዓመት የነበረው አየር ሁኔታ ተመችቶኝል። በውድድሩ በጣም ነው የተደሰትኩት።” ባለፈው ዓመት የበርሊን ማራቶን ውድድር የሴቶችን የማራቶን ክብረ ወሰን በከፍተኛ ልዩነት በማሻሻል ዓለምን ያስደነቀችው ትዕግሥት፣ በፓሪስ ኦሊምፒክ በጥቂት ልዩነት በሲፋን ተቀድማ የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያን ብታጣም በለንደን ማራቶን አሸናፊ ከመሆን ባሻገር ክብረ ወሰን ለማሻሻል በቅታለች።
ይህም ትዕግሥት አሰፋ ባለንበት ዘመን በዓለም የሴቶች የማራቶን ውድድር ዋነኛዋ አትሌት እንድትሆን በማድረግ በቀጣይ በሚኖራት ውድድር ሌላ ድል ሌላ ክብረ ወሰን እንደምታሻሽል ተጠባቂ አድርጓታል።
ሚያዝያ 19/2017 ዓ.ም. በተካሄደው የለንደን ማራቶን ውድድር አትሌት ትዕግሥት አሰፋ ቀዳሚ በመሆን አሸንፋለች።አትሌት ትዕግሥት ውድድሩን ሁለት ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ50 ሰከንድ በመግባት (2:15:50) እና ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ነው ያሸነፈችው። አትሌት ትዕግሥት ዛሬ ያስመዘገበችው ሰዓት በሴቶች ብቻ የተሮጠ የዓለም ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቦላታል።
በፓሪስ ኦሎምፒክ ሁለተኛ በመውጣት ብር ያገኘችው ትዕግሥት አሰፋ፣ በዛሬው የለንደን ማራቶን ከዚህ ቀደም በኬንያዊቷ ፔሬስ ጄፕቺርቺር የተያዘውን ፈጣን ሰዓት በ26 ሰከንድ በማሻሻል ማሸነፍ ችላለች።
ትዕግሥት “ባለፈው ዓመት [በለንደን ማራቶን] ሁለተኛ ነበር የወጣሁት፤ ስለዚህ በዚህ ዓመት ማሸነፌ በጣም ልዩ ነው። በጣም፣ በጣም ደስተኛ ነኝ” ስትል ለቢቢሲ ዋን ተናግራለች።
“ባለፈው ዓመት ከቅዝቃዜው ጋር በተያያዘ ትንሽ ችግር አጋጥሞኝ ነበር። እንዲሁም የእግሬ ጡንቻ ላይ ሕመም ነበረኝ። በዚህ ዓመት አየሩ በጣም ተስማምቶኛል” ስትል አክላለች።
“ሩጫው የተጠናቀቀበት መንገድ በጣም አስደስቶኛል።”
በዘንድሮው የለንደን ማራቶን ኬንያዊቷ ጄፕኮስፔ ሁለተኛ፣ ኔዘርላንዳዊቷ ሲፈን ሀሰን ደግሞ ሦስተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቅቀዋል።
ትዕግሥት ባለፈው ዓመት በለንደን ማራቶን ሪከርድ ለማስመዝገብ እንደምትሮጥ ተናግራ የነበረ ቢሆንም ሁለተኛ በመሆን ውድድሩን ጨርሳለች።
የፓሪስ ኦሊምፒክ ሻምፒዮኗ ሲፋን ሀሰን ዘንድሮ በተካሄደው የለንደን ማራቶን ሦስተኛ ሆና አጠናቅቃለች።
አትሌት ትዕግሥት አሰፋ ተወልዳ ያደገችው በአዲስ አበባ አቅራቢያ በምትገኘው ሆለታ ከተማ ነው።
አትሌት ትዕግሥት አሰፋ በ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ፣ አትሌት ሲፋን ሀሰንን ተከትላ ሁለተኛ ሆና በማጠናቀቅ ለኢትዮጵያ የብር ሜዳሊያ አምጥታለች።
ትዕግሥት ወደ አትሌቲክስ የገባችው በትምህርት ቤቶች መካከል በተደረጉ ውድድሮች እንደሆነ ተናግራ ለዚህም የሰውነት ማጎልመሻ መምህሯ አስተዋፅዖ ማድረጋቸውን ተናግራ ነበር።
ትዕግሥት በጀርመን በርሊን በተካሄደ 48ኛው የማራቶን ውድድር የዓለም የሴቶች ማራቶን ክብረ ወሰንን ከሁለት ደቂቃ በላይ በማሻሻል አሸንፋለች።
ለረዥም ጊዜያት የ800 ሜትር ሯጭ የነበረችው ትዕግሥት፣ ወደ ጎዳና ሩጫ ፊቷን ያዞረችው ዘግይታ ነው።በ2016 ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ወክላ በ800 ሜትር ተሳትፋለች።ሆኖም ከግማሽ ፍጻሜው ማለፍ ባለመቻሏ ከውድድሩ ውጪ ሆና ነበር።
ትዕግሥት ከ800 ሜትር በተጨማሪ በ400 ሜትርም ስትወዳደር ቆይታለች።አትሌቷ ቀደም ሲልም የግማሽ ማራቶን ውድድሮችን ለማሸነፍ በቅታለች። የዓለም የማራቶን ክብረወሰን ባለቤቷ ትዕግሥት አሰፋ በፓሪስ ኦሎምፒክ በ2 ሰዓት ከ22 ደቂቃ ከ58 ሰከንድ በመግባት ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ ይታወሳል።
የ2025 የወንዶች ለንደን ማራቶን ውድድር ኬንያዊው ሴባስቲያን ሳው በአሸናፊነት አጠናቋል። ኬንያዊው አትሌት ሴባስቲያን ሳው ውድድሩን 2:02:27 በመግባት በቀዳሚነት ሲያጠናቅቅ፣ ኡጋንዳዊው አትሌት ጃኮብ ኪፕሊሞ ሁለተኛ ኬንያዊው አትሌት ሙቲሶ ሙንያኦ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀዋል። ኢትዮጵያዊው አትሌት ታምራት ቶላ አምስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል።
የዓለም የማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤቷ በድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ስሟ ስለመስፈሩ ምን አለች?
አትሌት ትዕግሥት አሰፋ በሴቶች ማራቶን 2 ሰዓት ከ11 ደቂቃ ከ53 ሰከንድ በመግባት ባስመዘገበችው ክብረ ወሰን አማካኝነት ስሟ በዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ (ጊነስ ቡክ ኦፍ ዎርልድ ሪከርድስ) ላይ የሰፈረው እየተጠናቀቀ ባለው ዓመት ነው።
የዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ከቢኤም ደብሊው ማራቶን ጋር በመተባባር በ2024/25 በበርሊን በተዘጋጁት ውድድሮቸ ላይ ክብረ ወሰን ላሻሻሉ ስፖርተኞች የምስክር ወረቀት ሽልማት ሰጥቷል።
በአውሮፓውያኑ 2024/25 በጀርመን በርሊን በተካሄደው ማራቶን 11 ክብረ ወሰኖችን ለማሻሻል ታስቦ ስምንት መሳካቱን የዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ያሳያል።
አትሌት ትዕግሥት ከቢቢሲ ጋር በነበራት አጭር ቆይታ ወቅት “በሽልማቱ እና በዕውቅናው በጣም ደስተኛ ነኝ” ያለች ሲሆን፣ የሯሷን ክብረ ወሰን ማሻሻል እንደምትፈልግም ተናግራለች።
“ከዚህም በኋላ ሪከርዱን ከዚህ በበለጠ ማሻሻል እፈልጋለሁ. . .ችሎታው አለኝ፤ አቅሙም አለኝ። ስለዚህ ችሎታዬን አዳብሬ ከዚህ የበለጠ ሰዓት መሮጥ እፈልጋለሁ።”
የዓለም የሴቶች ማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤቷ አትሌት ትዕግሥት አሰፋ በፓሪስ ኦሊምፒክ 2 ሰዓት ከ22 ደቂቃ ከ58 ሰከንድ በሆነ ጊዜ በመግባት ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ለአገሯ የብር ሜዳሊያ ማስገኘቷ ይታወሳል።
ከ14 ዓመት በፊት ወደ ሩጫ ዓለም የገባቸው ትዕግሥት አሰፋ መስከረም 13/2017 ዓ.ም. በጀርመን በርሊን በተካሄደው 48ኛው የማራቶን ውድድር የዓለም ክብረ ወሰንን ከሁለት ደቂቃ በላይ በማሻሻል 2 ሰዓት ከ11 ደቂቃ ከ53 ሰከንድ መግባቷ ይታወሳል።
ይህ ከእሷ በፊት የነበረውን ያሻሻለችበት ከሁለት ደቂቃ የበለጠ የጊዜ ልዩነት በማራቶን ውድድር ላይ እምብዛም ያልተለመደ በመሆኑ ትዕግስት ከፍተኛ አድናቆትን ከማግኘቷ ባሻገር፣ ክብረ ወሰኑን ለማሻሻል ረጅም ጊዜ ሊወስድ ይችላል ተብሏል።
የ29 ዓመቷ አትሌት እንደ አውሮፓውያኑ በ2019 በተካሄደው የችካጎ ማራቶን በኬንያዊቷ አትሌት ብሪጊድ ኮስጌ ተመዝግቦ የነበረውን 2:14.04 ክብረ ወሰን ነበር ከሁለት ደቂቃ በላይ ያሻሻለችው።
አትሌት ትዕግሥት የዓለም ክብረ ወሰን መስከረም 20/2017 ዓ.ም. በጀርመን በርሊን ባዘጋጀው የእራት ግብዣ ላይ፣ ከተለያየ አገራት የመጡ ከ20 የማይበልጡ የተጋበዙ እንግዶች መገኘታቸውን ገልጻ የምስክር ወረቀቱም በዚያው ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተበረከተላት ለቢቢሲ ተናግራለች።
የዓለም ክብረ ወሰንን ካሻሻለች አንድ ዓመት የሞላት ትዕግስት የዓለም ድንቃ ድንቅ የምሥክር ወረቀቱን ለመስጠት ቀድም ብሎ የተዘጋጀ ቢሆንም እርሷ የውድድር ዝግጅት ላይ በመሆኗ መዘግየቱን ተናግራለች።
“እውነት ለመናገር ትልቅ ደስታ ነው የተሰማኝ። እንደ ማራቶን አትሌትም ትልቅ ደስታ ነው የፈጠረብኝ” ስትል ለመጀመሪያ ጊዜ በድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ስሟ በመስፈሩ ደስታዋ ከፍተኛ መሆኑን ገልጻለች።
በአሁኑ ጊዜ በእሷ የተያዘውን የራሷን ክብረ ወሰን ለማሻሻል ፍላጎት እንዳላት በተደጋጋሚ የምትናገረው ትዕግሥት አሰፋ፣ በማራቶን ከ2 ሰዓት ከ10 በታች መግባት ይቻላል የሚል እምነት እንዳላት ተናግራ ነበር።
ለረዥም ጊዜያት የ800 ሜትር ሯጭ ሆና የቆየችው ትዕግሥት፣ ወደ ጎዳና ላይ ሩጫ ፊቷን ያዞረችው በቅርቡ ነው።
በ2016 ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ወክላ በ800 ሜትር ተሳትፋለች። ሆኖም ከግማሽ ፍጻሜው ማለፍ ባለመቻሏ ከውድድሩ ውጪ ሆና ነበር።
ትዕግሥት ከ800 ሜትር በተጨማሪ በ400 ሜትርም ስትወዳደር ቆይታለች።አትሌቷ ቀደም ሲልም የግማሽ ማራቶን ውድድሮችን ለማሸነፍ በቅታለች።
የበርሊን ማራቶን እና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች
በዓለም አትሌቲክስ ውድድር ውስጥ ከፍተኛ የሚባለው የፕላቲኒየም ደረጃ ያለው የበርሊን ማራቶን በአውሮፓውያኑ 1974 የተጀመረ ሲሆን፣ የዓለም ቁንጮ ሯጮች የሚሳተፉበት ውድድር ነው።በጀርመን መዲና የሚካሄደው ውድድር ፈጣን ሰዓት ከሚመዘገብባቸው የማራቶን ውድድሮች መካከልም አንዱ ነው። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዚህ ውድድር በተለያዩ ጊዜያት ያሸነፉ ሲሆን፣ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ እና ቀነኒሳ በቀለ ቀዳሚዎች ናቸው።
በሴቶች በኩል ጌጤ ዋሚ ውድድሩን ለማሸነፍ የቻለች የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ስትሆን፣ ጌጤ በ2006 እና በ2007 (እአአ) ውድድሩን በተከታታይ አሸንፋለች።አፀደ ሃብታሙ፣ አበሩ ከበደ፣ ትርፌ ፀጋዬ፣ አሸተ በከሬ እና ጎይተቶም ገብረ ሥላሴ ውድድሩን ማሸነፍ የቻሉ ሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው። በኮቪድ ወረርሽን ምክንያት ውድድሩ እአአ በ2020 አልተካሄደም።
በአውሮፓውያኑ 2023 የበርሊን ማራቶን ውድድር 55 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ከ120 አገራት ተሳታፊ ነበሩ።
48ኛውን ቢኤምደብሊው የበርሊን ማራቶን አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በቦታው ተገኝተው ተከታትለውታል ተብሎ ይገመታል። በወንዶች ምድብ ኬንያዊው ኤሉድ ኪፕቾጌ የርቀቱን ክብረ ወሰን በማሻሻል ቀዳሚ ሆኖ አጠናቋል።
የ37 ዓመቱ ኬንያዊ ውድድሩን 2:01:09 በሆነ ሰዓት አሸንፏል። ሌላኛው ኬንያዊ ማርክ ኮሪር ሁለተኛ ሲወጣ ኢትዮጵያዊው ታዱ አባተ ሦስተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቋል።ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ውድድሩን አራት ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ነው።ኃይሌ እአአ ከ2006 እስከ 2009 (እአአ) በተከታታይ ለአራት ዓመታት ውድድሩን አሸንፏል።
“የራሴን የማራቶን ክብረ ወሰን ደግሜ የማሻሻል ዕቅድ አለኝ” አትሌት ትዕግሥት አሰፋ
አትሌት ትዕግሥት አሰፋ ተወልዳ ያደገችው ከአዲስ አበባ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች በምትርቀው ሆለታ ነው። ስድስት ልጆችን ለታደለው ቤተሰብ እርሷ የመጨረሻ ልጅ ናት።
ሆለታ ውስጥ አራዳ ምሥራቅ ሜዳ በሚባል ትምህርት ቤት የተማረችው ትዕግሥት፣ በትምህርት ቤት በሚደረግ ውድድር ነበር ወደ አትሌቲክሱ የገባችው።
በሩጫው 400 ሜትር፣ 800 ሜትር እንዲሁም ግማሽ ማራቶን ሮጣለች። አገሯን በአፍሪካ ሻምፒዮና፣ በኦሊምፒክ ወክላለች። አሁን ደግሞ ትዕግሥት በአስደናቂ የሰዓት ልዩነት የሴቶች ማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤት ሆናለች። አትሌት ትዕግሥት አስደናቂው ድሏ እና ተያያዥ ጉዳዮች ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርጋለች።
ወደ አትሌቲክሱ እንዴት አንደገባሽ ታስታውሻለሽ?
አትሌት ትዕግሥት፡ ማንንም አይቼ አይደለም አትሌቲክሱን የጀመርኩት። በአጋጣሚ ስፖርት መምህራችን፣ በስፖርት ክፍለ ጊዜ ላይ አይቶኝ ሩጫ እንድጀምር ይመክረኝ ነበር። እኔም የእርሱን ምክር ተቀብዬ ውድድር ላይ ተሳትፌ ጥሩ ሮጥኩኝ። እናም ብዙም ሳልቆይ ወደ ክለብ ገባሁ። በዚያ ነው የአትሌቲክስ ስፖርትን የጀመርኩት።
ወደ አትሌቲክሱ እንድትገቢ ምክንያት የሆኑሽን የስፖርት መምህርሽን ታስታውሻቸዋለሽ?
አትሌት ትዕግሥት፡ አዎ የስፖርት መምህሬ፣ መምህር ተክለማርያም ይባላሉ። እርሳቸው ናቸው መጀመሪያ ላይ ወደ ስፖርቱ እንድገባ ያደረጉኝ።
በወቅቱ አንቺ ላይ ምን የተለየ ነገር ታይቷቸው ይሆን?
አትሌት ትዕግሥት፡ የሚገርመው ሕጻን ሆኜ ራሱ ተራምዶ መሄድ አልችልም ነበር። ሱቅ ምናምን ስላክ በሩጫ ነበር የምሄደው። በጣም ቀጫጫ ነበርኩ። ሁሉም ቦታ በሩጫ ነው የምሄደው። መራመድን አላውቅም። . . .(ሳቅ) ያንን ያዩ ይመስለኛል።
ሩጫ ከጀመረሽ ስንት ዓመት ሆነሽ ማለት ነው?
አትሌት ትዕግሥት፡ በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2001 ነው የጀመርኩት። አሁን 13 ወይም 14 ዓመት ይሆነኛል ማለት ነው።
በጀርመን በርሊን የዓለም ክብረ ወሰንን ከሁለት ደቂቃ በላይ ነው ያሻሻልሽው። ያ ደግሞ በጣም ትልቅ ውጤት ነው። ሪከርዱ በዚያን ያህል ልዩነት ይሰበራል ብለሽ ነበር?
አትሌት ትዕግሥት፡ እውነቱን ለመናገር ያን ያህል ይሰበራል ብዬ አላሰብኩም። ነገር ግን ስሰራ የቆየሁት ልምምድ ሪከርድ ለማሻሻል ያለመ ነበር። በዚህ ልክ ግን እሰብረዋለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር። ዕቅዴ 12 እና 13 ቤት ለመሮጥ ነበር። ከአሠልጣኜም ጋር ተነጋግረን ስንሰራ የነበረው ያንኑ ነበር። በእርግጥ ጥሩ አቋም ላይ ነበርኩኝ። ግን በዚህ ልክ እሮጣለሁ ብዬ አላሰብኩም።
ከዚህ በኋላስ ይህንኑ ያንቺን ክብረ ወሰን ለማሻሻል ዕቅድ አለሽ?
አትሌት ትዕግሥት፡ በደንብ. . . በደንብ።
እስከ ስንት ድረስ? ለምሳሌ አሠልጣኝሽ ከ2፡10 በታች መግባት ይቻላል ይላል። አንቺ በዚህ ትስማሚያለሽ?
አትሌት ትዕግሥት፡ በደንብ እስማማለሁ። የተሻለ ልምምድ ከተሰራ ይሰበራል። ምክንያቱም ድካም ተሰምቶች አልነበረም የጨረስኩት። አቅም ነበረኝ። ትንሽ የዙሩ [ፔስ] አለመስተካከል ነበር። እሱ እሱን ካስተካከልን ከ2 ሰዓት ከ10 በታች ይሮጣል ብዬ አምናለሁ።
ሌላው ዓለም ሲያወራበት የነበረው ስለ ጫማው ነው። አንቺ ነሽ ለመጀመሪያ ጊዜ የሮጥሽበት። እንዴት ነው ይመቻል?
አትሌት ትዕግሥት፡ ጫማው በጣም ነው የሚመቸው። በጣም ነው የረዳኝ። በጣም አሪፍ ጫማ ነው።
ባለፉት 13 ዓመታት ከሮጥሽባቸው ጫማዎች በምን ይለያል?
አትሌት ትዕግሥት፡ ከዚህ በፊት የነበሩት ትንሽ ከባድ ናቸው። ይህ ግን በጣም ቀላል ነው። . . . ያው ማራቶን ይታወቃል ረዥም ርቀት ነው። በዚህ ውድድር ቀለል ያለ ጫማ ማድረግ ጥሩ ነው። ስለዚህም እኛ አድቫንቴጅ [ዕድል] ሰጥቶናል። ቀላል መሆኑ ይበልጥ ጠቅሞኛል ብዬ ነው የማስበው።
ምቾትስ አለው?
አትሌት ትዕግሥት፡ አዎ ምቾትም አለው፤ በጣም ቀላል ነው።
ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ በበርሊን ማራቶን ላይ አሸንፈሽ ነበር። ከዚያ ግን ጉዳት አጋጥሞሽ ነበር። ምንድን ነበር የደረሰብሽ ጉዳት?
አትሌት ትዕግሥት፡ ከበርሊን በኋላ ትንሽ ጉዳት አጋጥሞኝ ነበር። ለበርሊን ስዘጋጅ በጣም ከባድ [ኦቨር] ዝግጅት ሳደርግ ነው የነበረው። እግሬ ጉዳት ነበረው፤ ከበርሊን በኋላ እረፍት ሳላደርግ ወዲያው ወደ ሌላ ውድድር ነበር የሄድኩት፣ ማረፍ ነበረብኝ። ያ የለንደን ውድድር ላይ እንዳልሳተፍ አድርጎኛል።
በእርግጥ ትንሽ ጉዳት ነበር፤ ነገር ግን ዶክተሩ እንዳትሰለፊ፣ ይህ ትንሽ ጉዳት እየባሰ ከሚሄድ እዚችው ላይ ብናየው ይሻላል። ከፊታችን ኦሊምፒክ ስላለ ይህንን ጉዳት ብናገግም ይሻለል ብሎ መከረኝ። እኔም በዶክተሩ ሃሳብ ተስማምቼ የተወሰነ እረፍት አድርጌ፣ ፊቴን ወደ በርሊን ማራቶን ዝግጅት አዞርኩኝ። ስድስት ወር ነው የተዘጋጀሁት።
ለመጀመሪያ ጊዜ ከአገር ወጥተሽ የሮጥሽው የት ነው?
አትሌት ትዕግሥት፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአገር ወጥቼ የሮጥኩት ሱዳን ነው በአፍሪካ ሻምፒዮና ላይ። ነገር ግን በዚያው ወደ ቤኒን ሄደናል። በወቅቱ በ400 ሜትር ነበር አገር የወከልኩት።
ከዚያ በኋላ ኦሊምፒክ መጣ። ሪዮ ኦሎምፒክ እንዴት ነበር?
አትሌት ትዕግሥት፡ ኦሊሎምፒክ ላይ በ800 ነበር የተሳተፍኩት። በወቅቱ በጣም በጉዳት ላይ ነበርኩ። እግሬን በጣም ያመኝ ነበር። አኪለስ (ከቁርጭምጭሚቴ በላይ የሚገኝ ጅማት) በጣም ያመኛል። አጭር ርቀት ነው። 800 ሜትር በጣም ፈጣን ነው። በጣም የፍጥነት ልምምድ ነበር ስንሰራ የነበረው። በዚህም በጣም እግሬን እያመመኝ ነበር። ለእኔ በጣም ከባድ ነበር። በከባድ ሁኔታ ውስጥ ነው ያሳለፍኩት። ከዚያ በኋላም ወደ 800 አልተመለስኩም። እዚያ ላይ ነው ያቆምኩት።
ከዚያ በኋላም የተለያዩ ጉዳቶችን አጋጥመውሽ ነበር?
አትሌት ትዕግሥት፡ ከ800 ሜትር በቀጥታ ወደ ማራቶን ነው የገባሁት። ምክንያቱም ሌላ 10 ሺህ 5 ሺህ መሞከር አልቻልኩም። ምክንያቱም በስፓይክ (የመሮጫ ጫማ) መሮጥ አልቻልኩም። ስለዚህ ቀጥታ ነው ወደ ጎዳና ሩጫ የሄድኩት። ሰውነቴ ጫናውን መቋቋም አቅቶት የነበረው ሕመም ተባባሰብኝ።
ግማሽ ማራቶን ስፔን ቫሌንሺያ ላይ ልሮጥ ሄጄ [እኤአ 2019] እዚያ ላይ ተጎድቼ በክራንች ነበር የመጣሁት። ምንድን ነው ስህተቱ የምሮጥበትን ርቀት ስቀይር ቅደም ተከተሉን ያልጠበቀ ነበር። 10 ሺህ፣ 5 ሺህ መሥራት ነበረብኝ። ቀጥታ ከአጭር ርቀት ወደ ማራቶን ነው የገባሁት። ያ ትንሽ ሕመሜን አባብሶብኝ ያ ነው የተፈጠረው።
ቫሌንሽያ ላይ ውጤትሽ ምን ነበር?
አትሌት ትዕግሥት፡ አምስተኛ ነው የወጣሁት። እያመመኝ ነበር የሮጥኩት። በአንድ እግር ነው የሮጥኩት ማለት እችላለሁ። መቆም እስከማልችል ደርሼ ነው ውድድሩን የጨረስኩት። እና ከባድ ጊዜ ነበር።
ህመምሽ ምን ነበር?
አትሌት ትዕግሥት፡ የአኪለስ [Achiles] ታማሚ ነኝ። በጣም እየሄድኩ እያለ አኪለሴ በጣም አብጦ ስለነበር በምሄድበት ሰዓት ትናንሽ ስሮች አሉ፣ ወደ መሳሳብ እና መበጠስ ደርሰው ነበር። ወዲያው ውድድሩን ባቋርጠው ኖሮ ለዚያ ጉዳት አልጋለጥም ነበር።
ላለማቋረጥ ብዬ በከባድ ህመም ውስጥ ሁኜ ውድድሩን ጨረስኩት። ማቋረጥ ነበረብኝ፤ እኔ ግን ያንን ህመም ተቋቁሜ ውድድሩን ስጨርስ ግን መቆም አልቻልኩም ነበር፤ ቀጥታ በዊልቸር ነው ወደ ሕክምና የወሰዱኝ።
ከዚያ በኋላ የትኞቹ የጤና ባለሙያዎች ናቸው ከዚህ በኋላ መሮጥ አትችይም ያሉሽ?
አትሌት ትዕግሥት፡ ስፔን ነው። ከውድድሩ በኋላ ወዲያው እግሬ አብጦ ስለነበር፣ በአምቡላንስ ነበር ወደ ቀዶ ሕክምና ክፍል የሄድኩት።
ሐኪሞቹ ሲያዩት ከፍተኛ ጉዳት በመሆኑ እነርሱ ናቸው ከዚያ በኋላ ለማገገም እና ቁስሉ ወደ ቦታ ው ለመመለስ ጊዜ ይፈጃል፤ ብትሰሪበትም ጉዳቱ ከዚህ በኋላ ይብሳል የሚል ምክር የሰጡኝ።
እኔ ግን እንዳልሮጥ የሰጡኝም ምክር አልተቀበልኩትም ነበር። ማናጀሬም ዶክተሮቹ ያሉትን አልተቀበለውም። በዚህ አጋጣሚ ማናጀሬን ማመስገን እፈልጋለሁ።
ከዚያ በዚያው ሳምንት ድጋሚ ልታይ ወደ ጣልያን ነበር የሄድኩት። እነርሱም ተመሳሳይ ነገር ነበር የነገሩኝ። ጉዳቱ ከፍተኛ ነው። ተመልሰሽ ወደ ስፖርቱ የመመለስ ዕድልሽ በጣም ጠባብ ነው ነበር ያሉት።
ያንቺ ስሜት ምን ነበር እነርሱ ይህንን ሲሉሽ?
አትሌት ትዕግሥት፡ እኔ የሚገርምህ ተስፋ አልቆርጥም። ከዚህም በላይ ገጥሞኛል። ያንን ውድድር [ቫሌንሺያ ግማሽ ማራቶን] በአንድ እግር ነው ሮጬ የጨረስኩት ማለት እችላለሁ። በዚያን ጊዜ ለካ ጤነኛ ከሆንኩኝ፣ ጠንክሬ ከሠራሁ ታሪክ መሥራት ይችላል ብዬ ነበር ያሰብኩት።በዚያ ወቅት ሐኪሞች ከዚህ በኋላ ወደ ሩጫ አትመለሽም ሲሉኝ፣ ልቤ አልተቀበለውም ነበር። እዚያው ቁጭ ብዬ ለራሴ ሙሉ ጤናዬን አግኝቼ ታሪክ እሰራለሁ ስል ነበር።
ከዚያ በኋላ በክራንች ነበር የወጣሽው፤ ለማገገም ምን ያህል ጊዜ ፈጀብሽ?
አትሌት ትዕግሥት፡ ብዙም ጊዜ አልፈጀብኝም። ለአትሌት በክራንች መሄድ ከባድ ነው። ግን ምንድን ነው ያደረግኩት አልተቀመጥኩም። ሕመሙን የሚያሽለኝ እንደዋና ያለ ቀላል ልምምድ ስሰራ ነበረ። በሚገርም ሁኔታ በሁለት ወሩ ነው ለውጥ ያገኘሁት። ምክንያቱም እግሬ ታመመ እንጂ ጭንቅላቴ እና ልቤ አልታመመም ነበር። ያ ነው ቶሎ እንድድን ያደረገኝ።
በወቅቱ አንቺ ስለ ሕመምሽ የተሰማሽን ነገርሽኝ። ቤተሰቦችሽ ወይ አሠልጣኞችሽ እንዳንቺ ያስቡ ነበር?
አትሌት ትዕግሥት፡ አዎ አሠልጣኞቼም ችሎታዬን ስለሚያውቁ፣ በእኔ ላይ ትልቅ እምነት አላቸው። ከእኔ በላይ እንደውም በሰዓቱ እነርሱ ጠንካራ ነበሩ። “ያለሽ ችሎታ ዓለም ላይ ታሪክ ሳይሰራ ታሞ አይቀርም” ሲሉኝ ነበር። ቤተሰቦቼ በተለይ እናቴ፣ ባለቤቴ፣ አሠልጣኞቼ ሲሉኝ የነበረው ነገር ነው በይበልጥ ቶሎ አገግሜ እዚህ እንድደርስ ያደረገኝ። በጣም ነበር ሞራል ሲሰጡኝ የነበረው።
ከፍተኛ ጉዳት ደርሶብሽ በባለሙያዎች ከአሁን በኋላ መሮጥ አትችይም ተብለሽ ነበር። አሁን ደግሞ የዓለም ክብረ ወሰንን በእጅሽ አስገብተሻል። ሁለቱን አንዴት ነው የምታስተያያቸው?
አትሌት ትዕግሥት፡ ጉዳቴን መቼም የማልረሳው ነገር ነው። ውስጤ ተጽፎ የተቀመጠ ነገር ነው። ግን ዛሬ ይህችን ቀን ሳያት ደግሞ እንኳን ተጎዳሁ እንድል ነው ያደረገኝ። ምክንያቱም ባልጎዳ ኖሮ ይህችን ቀን አላያትም ነበር። ጠንክሬ አልሰራም ነበር።
በሕይወትሽ ተስፋ የቆረጥሽበት ጊዜ አለ?
አትሌት ትዕግሥት፡ እውነቱን ለመናገር ተስፋ የቆረጥኩበትን ጊዜ አላስታውስም።
እንደ ደራርቱ፣ ቀነኒሳ ያሉ አትሌቶችን ሳይ የሚጋሩት ባህሪ አለ፤ እልኸኝነት፤ የሚፈልጉትን ነገር እስኪያሳኩ ድረስ አለመበገር። አንቺስ ባህሪሽ አንዴት ነው?
አትሌት ትዕግሥት፡ በጣም እልኸኛ ነኝ። መሸነፍን አልወድም። (ሳቅ). . . እርሱ ነው መሰለኝ እንዲህ ጠንካራ እንድሆን ያደረገኝ። ያ እልህ ነው እንዲህ ጠንካራ ያደረገኝ። አልሸነፍም ባይ ነኝ። (ሳቅ)
ከቤተሰባችሁ ሌላ የሚሮጥ ሰው አለ?
አትሌት ትዕግሥት፡ በጭራሽ የለም። (ሳቅ)
አሁን ቀጣይ ዕቅድሽ ምንድን ነው? አሠልጣኝሽ ፓሪስ ኦሊምፒክ ነው ይላል።
አትሌት ትዕግሥት፡ እውነት ለመናገር እስካሁን አልወሰንንም። ለፓሪስ ኦሊምፒክ ግዴታ ሁለት ማራቶን መሮጥ ያለብኝ ይመስለኛል። አልወሰንንም። በእኛ ፍላጎት ቢሆን ጫና ሳናበዛ ቀጥታ ወደ ኦሊምፒክ ብንሄድ የሚል ነው።
ከአሠልጣኜ ጋር ያወራነው ግዴታ በዓመት ሁለት ማራቶን መሮጥ ስላለብኝ በፓሪስ ላይ ለመሳተፍ የለንደንን ማራቶን መሮጥ አለብኝ። ከአሠልጣኜ ጋር ያወራነው ግን ውድድር ሳናበዛ ቀጥታ ወደ ፓሪስ ዝግጅት ብንገባ ነው የተሻለ የሚሆነው እየተባባልን ነው። ምን አንደሚሆን እንግዲህ አንማከርበታለን።
ራስሽን የምታዝናኚው በምንድን ነው?
አትሌት ትዕግሥት፡ ፊልም በማየት እዝናናለሁ። ነገር ግን ልምምዴን በጥሩ ብቃት ሠርቼ የመጣሁ ቀን ነው በጣም ደስ የሚለኝ።

