አንጋፋው ደራሲ፣ ተርጓሚ፣ ተዋናይ፣ አዘጋጅ፤ መድረክ መሪ እና ፓለቲከኛ አርቲስት ደበበ እሸቱ በዛሬው ዕለት ነሐሴ 11/ 2017 በ83 ዓመቱ ከዚህ ዓለም ድካም ማረፉ ተሰምቷል።
አርቲስቱ ባደረበት ሕመም ምክንያት በተለያዩ ሆስፒታሎች ሕክምናውን ሲከተተል ቆይቶ ዛሬ ነሐሴ 11 ቀን 2017 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም ማረፋን አሐዱ ከቤተሰቦቹ አረጋግጧል።
አርቲስት ደበበ ለረጅም ዓመታት በተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ፊልሞች እና የመድረክ ተውኔቶች ላይ በብቃት የተወነ እና በኢትዮጵያ የኪነጥበብ ታሪክ ውስጥ የራሱን አሻራ ያሳረፈ አርቲስት ነበር።
በሀገር ፍቅርና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (የአሁኑ ብሔራዊ ቴአትር) መድረክ ላይ ለረዥም ዓመታት በተዋናይነትና በአዘጋጅነት የሰራ ሲሆን፤ በተለያዩ ፊልሞች ላይም በመሪ ተዋናይነት ተሳትፏል።
በሆሊውድ በተሰራው ‘ሻፍት ኢን አፍሪካ’ በተሰኘው ፊልም ላይ በመሳተፍ ስሙን በደማቁ የጻፈው አርቲስቱ፤ እንዲሁም ‘ዘ ሴይለር ፍሮም ጂብራልታር’፣ ‘ጉማ’፣ ‘ዘ አፍሪካን ስፓይ’፣ ‘ዜልዳ’፣ ‘ዘ ግሬቭ ዲገር’ እና ‘ዘ ግሬት ሪቤሊየን ‘ በእንግሊዘኛ ከሠራቸው ፊልሞች መካከል ይገኙበታል።
በተጨማሪም በእንግሊዘኛ የተፃፉ ተውኔቶች ላይም ተሳትፎ በብቃት የተወነ ሲሆን፤ ‘ዘ ጌም ኦፍ ቼዝ’ ላይ በትወና፣ ‘ኦቴሎ’ ላይ በመተወንና በማዘጋጀትም አሻራውን አሳርፏል።
በተጨማሪ በሬድዮና በቴሌቪዥን ሥራዎችም ላይ የተሳተፈ ሲሆን፤ ‘ያላቻ ጋብቻ’፣ ‘ሮሚዎና ዡልየት’ እና ‘ዳንዴው ጨቡዴ’ ከተወነባቸው ሥራዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
ለአርቲስት ደበበ እሽቱ በኪነጥበብ መስክ ላበረከተው አስተዋጽኦ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሐምሌ 13 ቀን 2015 የክብር ዶክትሬት ያበረከተለት ሲሆን፤ በተጨማሪም ለሙያ አስተዋጽኦው በአሜሪካ በአትላንታ ጆርጂያ ኖቬምበር 24 የደበበ እሸቱ ቀን ተብሎ እንዲሰየም የከተማው ምክር ቤት አጽድቋል።
አርቲስት ደበበ እሸቱ 4 ልጆች አባት የነበረ ሲሆን፤ 6 የልጅ ልጆችም አሉት።

