ላለፉት 43 ዓመታት ፣ በጋዜጠኝነት ያገለገለው ቀደምት ጋዜጠኛ ሙልጌታ ወልደሚካኤል ትናንት ጥቅምት 3 2017 ዓ•ም ከምሽቱ 5 ሰዓት ማረፉ ተሰምቷል።
የቀብር ሥነ ሥርዐቱም፣ ዛሬ ጥቅምት 4 2017 ደብረ ይድራስ ቅዱስ ጊዮርጊስ (ወይራ) ሰፈር ከቀኑ 8 ሰዓት ላይ ተፈፅሟል ።
የሚድያ ሰው ሙልጌታ ወልደሚካኤል፣ ከ1969 ጀምሮ በኢትዮጵያ ሬድዮ ከሪፖርተርነት እስከ አማርኛ ክፍል ኃላፊነት የደረሰ ታላቅ ባለሙያ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፣ በኢትዮጵያ ሬድዮ ከዛሬ 40 ዓመት በፊት አየር ሰዐት ወስዳ ፕሮግራም በምታስተላልፍበት ዘመን የፕሮግራሙ አዘጋጅ የነበረው ሙልጌታ ወልደሚካኤል ትጉህ እንደነበር ይነገርለታል።
በመቀጠልም የዜና ክፍልን በመቀላቀል ሙያዊ አደራውን ለመወጣት የቻለ ነው። በ1970ዎቹ አጋማሽ የኢትዮጵያ ሬድዮ የቅዳሜ መዝናኛ ፎርማትን ከቀረፁት ባለሙያዎች አንዱም ነበር።
የሚድያ ሰው ሙልጌታ ወልደሚካኤል የአማርኛ ክፍል ኃላፊ በመሆንም ወጣት ጋዜጠኞችን እየመራ፣ በማስተማር እና በማበረታታት ኃላፊነቱን ሲወጣ ነበር።
በ1983 የመንግስት ለውጥ ሲደረግ ከማስታወቂያ ሚኒስቴር ከተሰናበቱ 50 የሚድያ ሰዎች አንዱ ሙልጌታ ወልደሚካኤል ነበር፡፡
በ1984 ጦቢያ መፅሄት ስትመሠረትም፣ በአዘጋጅነት የሠራ ሲሆን በኃላም በማስታወቂያና ፕሮዳክሽን ኃላፊነት እስከ 1998 ድረስ አገልግሏል፡፡
ባለፉት 18 ዓመታትም፣ ከሚድያ ጋር በተያያዘ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል አቅሙን ሳይቆጥብ ያወጣ ሰው ነበር።
የሚድያ ሰው ሙልጌታ ፣ በአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ላይ ህይወት ታሪኩ የተቀመጠለት ሲሆን ባለፈው ሀሙስም ለተወዳጅ ሚድያ ቃለ -ምልልስ ሰጥቶ ነበር።
አቶ ሙልጌታ የመጨረሻ ኢንተርቪውን በሰጠበት ዕለት በርካታ ቁምነገሮችን አንስቶ ነበር፡፡ የ 3 ሴት ልጆች አባትና የ 5 ልጆች አያት የነበረው ሙልጌታ ከሰዎች ጋር የሚግባባ ባለሙያ ነበር።
ለመላ ቤተሰቡ እና ወዳጆቹ መፅናናትን እንመኛለን።

