የአፍሪካ ህብረት ይፋ ባደረገው አዲስ ሪፖርት፣ አህጉሪቱ በህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር (Illicit Financial Flows – IFFs) ምክንያት በየዓመቱ 88 ቢሊዮን ዶላር ገደማ እንደምታጣ አጋለጠ። ሪፖርቱ እንዳመለከተው፣ ይህንን ከባድ የሀብት ብክነት ለመግታት ላለፉት አስር ዓመታት የተደረገው ጥረት፣ በአፍሪካ ሀገራት መካከል ባለው የአቋም ልዩነት እና የቅንጅት እጦት ምክንያት “የተቀላቀለ ውጤት” ብቻ አስገኝቷል።
ይህ አዲስ የኪሳራ መጠን፣ ከዚህ ቀደም ከነበረው የ50 ሚሊዮን ዶላር ግምት በእጅጉ ከፍ ያለ መሆኑ የችግሩን ጥልቀት ያሳያል።
ሪፖርቱ ኢትዮጵያን በስም ከጠቀሳቸው ሀገራት መካከል ስትሆን፣ ምንም እንኳን ጥብቅ የባንክ እና የውጭ ምንዛሬ ቁጥጥሮች ቢኖሯትም፣ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል በቂ እንዳልሆኑ አመልክቷል።
በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ክፍተቶች ሲዘረዝር፦ የእውነተኛ የንግድ ባለቤቶች የመረጃ ቋት (beneficial ownership database) አለመኖርን ይጠቅሳል። ይህ ክፍተት፣ በሙስና የተሳተፉ ሰዎች እውነተኛ ማንነታቸውን በሌሎች ስም እንዲደብቁ ያስችላቸዋል። ሌላው ጥፋተኛ የተባሉ ግለሰቦችን እና ኩባንያዎችን የሚቀጣ ውጤታማ የማዕቀብ ስርዓት አለመኖር ነው። ይህም አንድ ጊዜ በህገ-ወጥ ድርጊት የተገኘ ሰው፣ ቅጣት ቢቀበል እንኳ በቀላሉ ወደ ተመሳሳይ ወንጀል እንዲመለስ እድል ይሰጠዋል።
ሪፖርቱ እነዚህ ክፍተቶች በተለይ ግልጽነት በጎደለው የኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ ውስጥ በስፋት እንደሚታዩ እና ለከፍተኛ የሀብት ብክነት እየዳረጉ እንደሆነ ጠቁሟል።
ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውሩ ከሚፈጸምባቸው መንገዶች መካከል፣ ሁለት ሶስተኛውን ድርሻ የሚይዘው በንግድ እንቅስቃሴዎች (እንደ የዝውውር ዋጋ ማዛባት፣ ኢ-ፍትሃዊ ስምምነቶች እና የታክስ ስወራ) እንደሆነ ሪፖርቱ አብራርቷል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን፣ የአፍሪካ ሀገራት የመንግስት ተቋማት በመካከላቸው ያለውን የቅንጅት ችግር በመቅረፍ እና የመረጃ ልውውጥን በማጠናከር ይህንን የሀብት ዝርፊያ እንዲያስቆሙ ምክረ-ሀሳቡን አቅርቧል።

