የኢራቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙሐመድ ሺአ አል ሱዳኒ አለም አቀፍ ወታደሮች በኢራቅ አሁን የሚቀመጡበት ምንም ምክንያት የለም ብለዋል፡፡
ስለሆነም አሜሪካ ጦሯን ከኢራቅ ምድር ስታስወጣ ብቻ ኢራቅም ሚሊሻዋን ትጥቅ እንዲፈታ ታደርጋለች ብለዋል፡፡ በሀገሪቱ አሁን ምንም አይነት ስጋት በሌለበት ሁኔታ ከተለያዩ ሀገራት የተወጣጡ ጥምር ጦር በአሜሪካ እየተመራ በኢራቅ መኖሩ ምክንያት የሌለው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
በ2024 በፕሬዝዳንት ባይደን የስልጣን ዘመን የአሜሪካ እና የኢራቅ ተደራዳሪዎች የአሜሪካ ጦር ለቆ እንዲወጣ የሚያስችል ስምምነት ተፈርሞ እንደነበር ሚድል ኢስት አይ አስታውሷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አል ሱዳኒ የሚሊሻ አባላቱ ትጥቃቸውን ከፈቱ በኋላ ወደ መንግስት የጸጥታ ሃይል አባላት እንደሚቀላቀሉ ተናግረዋል፡፡
የኢራቁ ሚሊሻ ጉዳይ ከሊባኖሱ ሄዝቦላህ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው፡፡ በዚህ ስዓት ሊባኖስ ሄዝቦላህን ትጥቅ እንድታስፈታ የተስማማች ቢሆንም ሂደቱ ግን አስቸጋሪ ሁኔታ እንደገጠመው እየተነሳ ነው፡፡
እነዚህን ሁለቱን ሀይሎች ጨምሮ ሁቲን እንዲሁም ሃማስን በገንዘብ የምትረዳውም ሆነ በስልጠና እና በመሳሪያ የምታስታጥቀው ኢራን ነች፡፡
የኢራቁ ሚሊሻ በ2024 የአሜሪካ ወታደሮች በጆርዳን ጥቃት ሲደርስባቸው ከጀርባ ነበር፡፡ በተጨማሪም በእስራኤል ላይ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ላይም ተባባሪ ነው፡፡ ይህን የሚያደርገው ለፍልስጤማዊያን አጋርነቱን ለማሳየት በሚል ነው፡፡
የሊባኖስ ጦር በአብዛኛው ደቡባዊ ሊባኖስ ሄዝቦላህን ትጥቅ እያስፈታ መሆኑን የሚገልጽ መረጃ እንዳለው ሚድል ኢስት አይ ዘግቧል፡፡
የሲቪሉ አስተዳደር ቡድኑ የታጠቃቸውን ከባድ መሳሪያዎች ለጦሩ እንዲያስረክብ ድርድር ላይ ነው ቢባልም፤ቡድኑ ግን በዚህ አልተስማም ተብሏል፡፡
ቡድኑን በሃይል ትጥቁን እንዲፈታ ከማደረግ ይልቅ ሃብታም ገልፉ ሀገራት የገንዘብ ስጦታ እንዲሰጣቸው በማድረግ ትጥቅ ማስፈታት ይቻላል የሚል ሃሳብ ስለመቅረቡም ከዘገባው ላይ ተመልክተናል፡፡
በኢራቅ ታዋቂው ሃይል ከመንግስት ገንዘብ ያገኛል፡፡ በሱዳኑ አስተዳደር ለ150ሺ ለሚደርሱት አባላቱ ተጨማሪ 700 ሚሊዮን ዶላር በሦስት ዓመት በጀት ውስጥ ተመድቦለታል፡፡//

