በሞት ከተቀጡት መካከል አንዱ በማዕከላዊ ኢስፋሃን በሚገኘው ናታንዝ የኒውክሌር ተቋም አካባቢ የደህንነት መረጃዎች ሲሰበስብ ነበር መባሉን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የመገናኛ ብዙኃኑ ዘገባ እንደሚያመለክተው ያግሆብ ካሪምፖር እና ናስር ባካርዛዴህ የተባሉት ኢራናውያን የደኅንነት መረጃዎችን በማቀበል ከእስራኤል የስለላ ተቋም ጋር በመተባበራቸው በስቅላት ተቀጥተዋል።
ካሪምፖር ወሳኝ የደኅንነት መረጃ ለሞሳድ ባልደረባ ማቀበሉ ሲገለጽ፣ ባካርዛዴህ ደግሞ ስለ መንግሥት እና የሃይማኖት መሪዎች እንዲሁም በናታንዝ ስለሚገኘው የኒውክሌር ተቋም መረጃዎችን ሲሰበስብ ነበር የሚል ክስ ቀርቦበታል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢራን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ቴህራን ከብሔራዊ ደኅንነት ጋር በተያያዘ ወንጀል 21 ሰዎችን በሞት መቅጣቷን እና ከ4,000 በላይ ማሰሯን ረቡዕ ዕለት አስታውቋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኃላፊ ባወጡት መግለጫ ከተገደሉት መካከል ዘጠኙ በጥር ወር በተካሄደው የተቃውሞ ሠልፍ ጋር በተያያዘ የተቃዋሚ ድርጅቶች አባል ናቸው በሚል ሲወነጀሉ፣ ሁለቱ ደግሞ በአገር ክህደት ተስሰው መገደላቸውን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እስራኤል ዘመናዊና ጥራት ያላቸው የጦር መሣሪያዎችን እና ተያያዥ ቁሳቁሶችን እንድትገዛ የቀረበውን የሽያጭ ጥያቄ ማጽደቁን አስታውቋል።
ይህ የጦር መሣሪያ ሽያጭ በግምት 992.4 ሚሊዮን ዶላር ያወጣል ተብሎ የሚገመት ሲሆን፣ ግዢው የእስራኤልን የመከላከያ አቅም ለማጠናከርና በቀጣናው ያለውን ወታደራዊ ሚዛን ለመጠበቅ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ለኮንግረስ ባቀረበው ማሳወቂያ መሰረት፣ ይህ ስምምነት የአሜሪካን የውጭ ፖሊሲ እና ብሔራዊ ደህንነት ግቦችን የሚደግፍ ነው።
ስምምነቱ ሚሳኤሎችን የቴክኒክ ድጋፎችን እና የሎጅስቲክስ አገልግሎቶችን በማካተት፥ ትግበራውም በዋናነት በታዋቂው የጦር መሣሪያ አምራች ኩባንያ ቢኤኢ ሲስተምስ በኩል የሚከናወን ይሆናል ነው የተባለው።
ይህ ውሳኔ በምስራቅ መካከለኛው ቀጣና ያለውን ወቅታዊ ውጥረት ተከትሎ የመጣ መሆኑ የበርካታ ወገኖችን ትኩረት ስቧል።//
ኢራን ለእስራኤል ሲሰልሉ ነበር ያለቻቸውን ሁለት ሰዎች በሞት ቀጣች

