የኢራን ስፖርት እና ወጣቶች ሚኒስትር አህመድ ዶኒያማሊ አገሪቱ በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ላይ ልትሳተፍ እንደማትችል አስታውቀዋል።
ኢራን በመጪው ሰኔ ወር በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ አዘጋጅነት በሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ላይ እንደምትሳተፍ ተገልጾ ነበር።
ኢራን ከኒውዚላንድ፣ ቤልጂየም እንዲሁም ግብጽ ጋር ግጥሚያዎችን በሎስ አንጀለስ እና ሲያትል እንደምታደርግ የወጣው መርሐ ግብር ያሳያል።
አሜሪካ እና እስራኤል አገሪቱ ላይ ጥቃት ፈጽመው የአገሪቱን የበላይ መሪ ጨምሮ ከፍተኛ ባለሥልጣኖችን እና ወታደራዊ መሪዎችን መግደላቸውን ተከትሎ የአገሪቱ ተሳትፎ ጥያቄ ውስጥ ወድቋል።
ረቡዕ ዕለት የፊፋው ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ኢራን መሳተፍ እንደምትችል እንዳረጋገጡላቸው ተናግረው ነበር።
የፊፋው ፕሬዝዳንት በኢንስታግራም ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ከትራምፕ ጋር ተገናኝተው ስለ ዓለም ዋንጫ ዝግጅት መወያየታቸውን ጠቅሰዋል።
ነገር ግን ዶኒያማሊ ማክሰኞ ከኢሪብ ስፖርት ኔትወርክ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ይህ ብልሹ መንግሥት መሪያችንን ከገደለ በኋላ በምንም ዓይነት ሁኔታ በዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ ተስማሚ ሁኔታዎች የሉንም።
“ልጆቻችን ደህንነታቸው የተጠበቀ አይደለም፤ እና ልንሳተፍበት የምንችልበት ሁኔታም የለም።”
አክለውም “ባለፉት ስምንትና ዘጠኝ ወራት ውስጥ ሁለት ጦርነቶች ተጭነውብናል፤ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ተገድለዋል፤ ሰማዕት ሆነዋል። ስለዚህ በእርግጠኝነት የመሳተፍ እድል የለንም” ብለዋል።

