ኢራን ወደ እስራኤል በተኮሰችው ባላስቲክ ሚሳኤል ቢያንስ 16 ሰዎችን አቆሰለ

ቴላቪቭን ኢላማ ያደረገው የኢራን ጥቃት በርካቶችን ማቁሰሉ ሲነገር፤ሄዝቦላህም ወደ ሰሜን ቴላቪቭ ሮኬቶችን መተኮሱ ተነግሯል፡፡

የእስራኤል ጦር ከየመኑ ሁቲ የተተኮሱ ሚሳኤሎችን ማክሸፉንም ገልጻል፡፡ ሁቲ የአሁኑን ጦርነት በይፋ የተቀላቀለው ባለፈው ቅዳሜ እለት በርካታ ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል በመተኮስ ነው፡፡ከየመን የዛሬውን ጥቃት ጨምሮ ወደ እስራኤል ሲተኮስ ለአራተኛ ጊዜ ነውም ተብሏል፡፡ ሁቲ ዲሞናን ጨምሮ ደቡባዊ የእስራኤል ክፍልን በማጥቃት ነበር በይፋ ከኢራን ጎን በመሰለፍ ጦርነቱን መቀላቀሉን ያስታወቀው፡፡

ሁቲ አሁን የጀመረውን ጥቃቱን የሚያቆመው እስራአል የጀመረችውን ወረራ ስታቆም ብቻ እንደሆነ በመግለጽ ላይ መሆኑን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ቡድኑ አክሎም ወታደራዊ ውጥረቱ እየጨመረ ከሄደም የባብል ኤል መንደብን መተላለፊያ ለመዝጋት እንደሚገደድም አስታውቋል፡፡የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋቱን ተከትሎ በመላው ዓለም የተፈጠረው ከፍተኛ ጫና ሳይቃለል ተጨማሪ ሌላ ጫና ሊፈጠር ነው በሚል በከፍተኛ ሁኔታ ተሰግቷል፡፡

አሜሪካም ሆነች እስራኤል የጦርነቱ ግቦች ከሞላ ጎደል እየተሳካ መሆኑን በየፊናቸው በመግለጽ ላይ ቢሆኑም እስራኤል ግን በይፋ ጦርነቱ መቼ እንደሚጠናቀቅ ያለችው ነገር የለም፡፡በርግጥ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሦስት ወይንም በአራት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ኢራን ከስምምነት ላይ ደረሰችም፤አልደረሰችም ጦርነቱ ይጠናቀቃል እያሉ ነው፡፡ኢራን በገልፍ ሀገራት ላይም ሆነ በእስራኤል ላይ የምታደርሰውን ጥቃት ለተመለከተ ግን ጦርነቱ በጥቂት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል የሚል መደምደሚያ ላይ ለመድረስ ያስቸግራል ተብሏል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታም የገልፉ ሀገራት አሜሪካ በኢራን ላይ የምታደርሰውን ጥቃት አጠናክራ እንድትቀጥል ፍላጎት እንዳላቸው ይገለጻል፡፡ይህ በዚህ እንዳለ የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ኢራን በዚህ ስዓት ከአሜሪካ በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ መልዕክቶች እየደረሷት ነው ብለዋል፡፡ ነገር ግን ይህንን ድርድር ብለን መጥራት አንችልም እስካሁንም ድርደር የለም በማለት ገልጸዋል፡፡እስካሁንም የተወሰኑ መልዕክቶም በልዩ መልዕክተኛው እስቲቭ ዊትኮቭ እንዲሁም ጥቂት መልዕክቶች ደግሞ ወዳጅ በሆኑ ሀገራት በኩል ደርሶናል ብለዋል፡፡

ከአሜሪካ በኩል ስለ ቀረበው ባለ 15 ነጥብ የሰላም እቅድም የሰጠነው ምላሽ የለም ብለዋል፡፡ ሚኒስትሩ አክለውም ከአሜሪካ ጋር ምንም አይነት በመልካም የሚነሳ የድርድር ተሞክሮም የለንም ነው ያሉት፡፡በሁለታችን መካከል ያለው የመተማመን ደረጃም ዜሮ ነው ብለዋል፡፡ አባስ አራግቺ በተጨማሪም የሆርሙዝ ሰርጥ አሁንም ቢሆን ከቴህራን ጋር ጦርነት ላይ ላልሆኑ ሀገራት ክፍት እንደሆነ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የሆርሞስ ሰርጥ የሚገኘው በኢራን እና በኦማን ውሃ ላይ እንጂ በዓለም አቀፍ ውሃ ላይ አይደለም ፤ስለሆነም ይህንን ውሃ በእስትራቴጂካዊ መንገድ የመጠቀም መብቱ የእኛ እና የኦማን ነው ብለዋል፡፡ አሁን እየሆነ ያለውም ከእኛ ጋር በጦርነት ላይ ላሉት ሀገራት ውሃችንን ለንግዳቸው እንዲጠቀሙ አንፈቅድም ወዳጆቻችን ግን መጠቀማቸውን ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡አባስ አራግቺ የኢራን ጦር የአሜሪካን የምደር ዘመቻ በፍጹም እንደማይፈሩም ተናግረዋል፡፡ አሁን የሚመጡ ከሆነ እየጠበቅናቸው ነው፤ጦርነቱን የጀመርነው እኛ አይደለንም እያደረግን ያለነው እራሳችንን መከላከል ነው እሱን ማደረጋችንን ደግሞ እንቀጥላለን አሜሪካ ግን እንዲህ አይነቱን ስህተት ትሰራለች የሚል ተስፋ የለኝም ብለዋል፡፡

ሙሉ በሙሉ ከስምምነት ላይ መድረስ የሚቻለው አሜሪካ እና እስራኤል እየፈጸሙት ያለውን ጥቃት ሙሉ በሙሉ ሲያቆሙት ብቻ ነው ብለዋል፡፡ለምድር ዘመቻ ከመጡ ግን እንዲያውም በእግረኛ ጦሩ የተሻለ ውጤት እናገኛለን ሲሉ ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል፡፡//

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe