ኢራንና እስራኤል መጨረሻ ምንድነው?(አስፈሪ ቃሎች፣ ግራ-አጋቢ ትንቢቶች)

የዚህ መፅሐፍ ደራሲ ማርክ ሂችኮክ አሜሪካዊ ነው። በዳላስ የሚኖር የመንፈሳዊ ትምህርት ዶክተር፣ ተመራማሪና ደራሲ ፕሮፌሰር ነው። ስለ ዓለም ፍፃሜ የሚተነትኑ 20 መፅሐፎችን ፅፏል። የዓለምን መጨረሻ የሚያውቀው አሁን በምድር ላይ በህይወት ያለ ብቸኛው ሰው ነው እየተባለ እስከመደነቅም ደርሷል።

በዚህ መፅሐፉ ስለ ኢራንና እስራኤል በቀዱስ መፅሐፉ የተነገሩ ትንቢቶችን ግልፅልፅ እያደረገ ከጂኦግራፊ፣ ከታሪክ፣ ከሚሊቴሪ፣ ከኢኮኖሚ፣ እና ከሐይማኖት አንፃር እየመረመረ ትርጉማቸውን ይነግረናል። ኢራን በቅዱስ መፅሐፉ ፐርሺያ ተብላ የምትገለፅ ጥንታዊት ልዕለ ኃያል ሀገር እንደሆነች አይክድም ደራሲው። ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ331 ዓመተ ዓለም ቀደም ብሎ በነበሩት 200 ዓመታት – መላውን ዓለም በኃይሏ አስገብራ በበቸኝነት የገዛችው ፐርሺያ (ያሁኗ ኢራን) መሆኗን ከታሪክና ከቅዱስ መፅሐፉ ማስረጃዎችን እየጠቀሰ ያስረዳል። ልክ በቅዱስ መፅሐፉ በትንቢተ ኢሣያስ እንደተተነበየው ግን፣ ፐርሺያ በግሪኮች ተወግታ ከልዕለ-ኃያልነቷ ተፈነገለች! ቀስ በቀስም ከታሪክ መዝገብ እየተፋቀች ከ4ኛው ክፍለዘመን በኋላ የሮማ ኢምፓየር ስም ሲገንን የኢራን ስም ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን የሰፈር ተደባዳቢነት ተርታ ወረደ፣ ተዋረደ፣ ተረሳች!

ይህ የዓለም ፍፃሜ ነጋሪ ፕሮፌሰር፣ አሁን በኢራንና በእስራኤል መካከል የሚነሳ፣ መካከለኛው ምሥራቅን ብቻ ሳይሆን መላውን ዓለም የሚንጥ አንድ እጅግ አደገኛ ጦርነት እንደሚቀሰቀስ በመተንበይ የፃፈው የዛሬ 13 ዓመት ነው። በ2013 በፈረንጆቹ አቆጣጠር። የተናገረው ትንቢት ጊዜውን ጠብቆ ተፈፀመ። እስራኤልና አሜሪካ ተጋግዘው ኢራንን ይወጓታል ነበር ያለው። ሆነ። ይሄ የአሜሪካ መንፈሳዊ ተመራማሪና የአርማጌዶን ጠንቋይ የተነበየው ግን ይሄንን ብቻ አይደለም። ኢራን እጇን በኒውክሊየር ጦርመሣሪያ ላይ ለማሣረፍ ዕድሉን ካገኘች፣ በተደጋጋሚ በመፅሐፍ ቅዱስ የተነገረው፣ እና በኢራን መንፈሳውያን መሪዎች በየዘመኑ በተደጋጋሚ የሚታመንበት ትንቢት ይፈፀማል። ያ ትንቢት የዓለም መጨረሻን የምናይበት የፍፃሜ መባቻ መከሰት ነው! ኢራኖች ሁሌም ራሳቸውን የዓለም የመጨረሻዎቹ ትንቢት አስፈፃሚዎች ወይም ፈፃሚዎች አድርገው ይቆጥራሉ። ከልባቸውም ያምናሉ ይላል ይህ ፕሮፌሰር ጠንቋይ ማስረጃ እያጣቀሰ። በዚህም የተነሳ በቅዱስ መፅሐፉ እንደተነገረው ኢራን የኒውክሊየር ቦምብ ሠርታ ከጨረሰች፣ ያለ ጥርጥር እስራኤል ላይ ታፈነዳዋለች! እና የመጨረሻውን የፍፃሜውን ጦርነት (ማለትም አርማጌዶንን) ትቀሰቅሳለች! ቀስ በቀስ የዓለም ሀገሮች ሁሉ በሁለት ጎራ ተከፍለው በአርማጌዶኑ ውስጥ ገብተው ይተላለቃሉ!

ይህ አሜሪካዊ የዓለም ፍፃሜ ሳይንሳዊ ጠንቋይ – ፕሮፌሰር ማርክ ሂችኮክ – ከዘረዘራቸው ትንቢቶች መሐል በግሌ ያስደነገጠኝን ልናገር! ለሁለተኛ ጊዜ በአሜሪካዊ ምሁር መፅሐፍ በቁምነገር ተከትቦና ተተንትኖ ሳገኘው ነው! ይሄ ትንቢት ምንድነው? ትንቢቱማ – በፍፃሜው ጦርነት ኢትዮጵያ የምትሰለፈው ከእስራኤል ጋር ሳይሆን፣ ከኢራን ጎን ነው!! እኛ ኢትዮጵያውያን ትንቢቱ ሲፈፀም፣ ለኢራን ተደርበን፣ እጅግ ግዙፍ ሠራዊት አሰልፈንና ግዙፍ የጦር መሣሪያዎችን ታጥቀን እስራኤልን ለመውጋት በሆታ እንነቃነቃለን!! ፐርሺያ፣ ኢትዮጵያ እና ፑት – ሶስቱ ሀገሮች ያለ የሌለ ኃይላቸውን አሰባስበው እሰራኤል ላይ በጋራ ይዘምታሉ!!! የእስራኤልም ከተሞች በሚደርስባቸው ፍንዳታ የተነሳ በእሣት እንደገባ ነሃስ ይቀልጣሉ። ግድግዳዎቿ ይደረመሳሉ። እስራኤላውያን እንደ ገለባ ይሆናሉ። የተረፉት ይበተናሉ። ይህ የእስራኤል አስከፊ አወዳደቅ የሚቆየው ግን ለተወሰነ ጊዜ ነው! ከዚያስ? ትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ 7ን እና ትንቢተ እዝቅኤል ምዕራፍ 38 እና 39ን ተመልከት!! ይሄ የአሜሪካ ጠንቋይ ፕሮፌሰር ለእነዚህ የመፅሐፍ ቅዱስ የዓለም ፍፃሜ ትንቢቶች ለየብቻ ምዕራፍ ሰጥቷቸዋል። እና ደሞ ምን ይልሃል? –

በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወደ 1,000 የሚሆኑ ትንቢቶች አስቀድመው ተነግረዋል። ከእነዚህ ውስጥ ግማሾቹ (ወደ 500 የሚደርሱት) ያለምንም መዛነፍ፣ እያንዳንዷ ነጥብ ትንቢት ሳትቀር፣ ቃል-በቃል ተፈፅመዋል!! እና? እናማ የቀሩት 500ዎቹ ቃል-በቃል እንደሚፈፀሙ ቅንጣት ጥርጣሬ እንዳይኖርህ እያለ ነዋ የሚመክርህ!! በዳንኤልና በኢሣያስ ትንቢቶች መሠረት፣ እስራኤልን የሚረዳ እና ከኢራንና ከኢትዮጵያውያን መንጋጋ የሚያላቅቃት አንድ ታላቅ ኃያል ከሮማ ይነሳል!!! ለ2 ዓመታትም ከእስራኤል ጎን ቆሞ እነ ኢራንን በኃይልና በብርታት ይዋጋል! እና በፈጣሪ ትንቢት መሠረት፣ ቃሉ ይፈፀም ዘንድ፣ በእሣት አንፍሮ፣ ወደ አመድነት ይቀይራቸዋል!! እንዲያውም ትንቢተ እዝቅኤል ላይ እስራኤል ከዚህ ድል በኋላ የረገፉትን ጠላቶቿን አስከሬን ከየወዳደቁበት ሰብስባ ለመቅበር፣ 7 ወር ሙሉ ይፈጅባታል ይላል!! ከዚያ ደሞ ለቀጣዮቹ 7 ዓመታት የእስራኤል ህዝብና መሪዎች ሳያርሱ፣ ሳይዘሩ፣ ሳያጭዱ ለሰባት ዓመታት ሥጋና ጮማ እየቆረጡ፣ ደም እንደ አረቄ እየጠጡ፣ ከጠላቶቻቸው የማረኳቸውን ጠብመንጃዎች እያነደዱ ቤታቸውን እያሞቁ… እግራቸውን ሰቅለው በደስታና በተድላ ወደ ምድራቸው ተሰብስበው ይኖራሉ!! የአምላክንም ታላቅነት ያያሉ። ከዚያ ግን ዓለም ሁሉ ትናወጣለች። ምድር በቀውስ ትሞላለች። ወንድሞች በወንድሞች ላይ ይነሳሉ። ሰዎች እርስ በርሳቸው ይጠላላሉ፣ ይዋጋሉ፣ ይጫረሳሉ። ጥበብና ማስተዋል አፈር ድሜ ትግጣለች። እና የመጨረሻውን የፍረድ ቀን መድረስ የሚያበስረው መለከት ነፊ እንደ ዕድር ነጋሪ ጡሩምባውን እየነፋ ይመጣል! የሰው-ልጅ (the Son of Man) ነው የዓለምን ፍፃሜና የታላቁን አምላክ ለፍርድ መምጣት ሊያውጅ ወደ ምድር የሚመጣው!!

ፕሮፌሰር ማርክ ሂችኮክ ይህን ሁሉ የትንቢት መዓት ከቅዱስ መፃህፍት እያጣቀሰና ከመድሪቱ ፖለቲካና ታሪክ ጋር እያዛነቀ ከተረከ በኋላ፣ አንድ ግልፅ የማይሆንልኝ – እና የሚያጠራጥረኝ ነገር – ሌሎች ብዙዎች በእዝቅኤልና በዳንኤል ትንቢት በስም ሲጠቀሱ፣ ሀገሬ አሜሪካ ግን በስም አልተጠቀሰችም! /እና የአሜሪካ ዕጣፈንታ ምን ሊሆን ነው? እያለ ይጨነቃል!/ መልሱንም ከሁለት ነገሮች አንዱ ነው የሚፈጠረው በማለት ያቀርባል፦ አንድም/ ነብያቱ አሜሪካን በፍፃሜው ጦርነት ትንቢታቸው አንድም ቦታ በስም ያልጠቀሷት፣ አሜሪካ ከፍፃሜው ጦርነት በፊት፣ ምናልባትም በኒውክሊየር ውጊያ፣ ከምድረገፅ ጠፍታ የተረሳች ሀገር ስለምትሆን ይሆናል! ምናልባት አሜሪካ የዓለም ፍፃሜን ሳታይ ከምድሪቱ የምትሰናበት ጊዜያዊ ልዕለ-ኃያል ነች! ሁለትም/ ምናልባት ግን በዓለም ፍፃሜ ከሮማ ምድር በመነሳት፣ ከእስራኤል ጎን ተሰልፎ ይዋጋና ያድናታል ተብሎ የተፃፈለት የአርማጌዶኑ ባለድል… ምናልባት አሜሪካ ብትሆንስ? ይላል። ብትሆንስ? አሜሪካውያንና መሪዎቿ በአብዛኛው ከአውሮፓ ምድር ፈልሰው የመጡ መሆናቸውን ስናጤን፣ የዓለም የፍፃሜ ጦርነት ከተቀሰቀሰም፣ ያለ ጥርጥር አሜሪካውያን የሚሰለፉት፣ በሐይማኖትም፣ በጂኦግራፊም፣ በታሪክም፣ በኢኮኖሚም ከማይመስሏቸውና ከማይጣመሯቸው ከእስያኖች፣ ከአፍሪካኖችና ከመካከለኛው ምሥራቆች ጋር ሳይሆን… ከአውሮፓና ሜዲትራኒያኖች ጋር ነው የሚሆነው!! ይህ ከሆነ most probably በቅዱስ መፅሐፉ ከሮማ የሚነሳው ኢራንንና አጋሮቿን ኢትዮጵያንና ፑትን ድል የሚያደርገው ልዕለ-ኃያል፣ ሌላ ሳይሆን ራሷ አሜሪካ ነች!!

ወንድሜ፣ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ በወታደራዊው ሶሻሊስት መንግሠት እጅ በምትተዳደርበት የደርጉ ዘመን ላይ የተፃፈውን አንድ የዓለምን ፍፃሜ የሚናገር የምዕራባውያኑን መፅሐፍ ሳነብም፣ ያኔም፣ የዓለም የፍፃሜ ጦርነት አርማጌዶን የሚነሳው ከመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ እንደሆነና፣ ኢትዮጵያ ደሞ ኢራንን ለመደገፍ እንደምትዘምት ተደርጎ የተተነተነውን አንብቤ ነበር። ያው ዘመኑ ባላጋራ ርዕዮተዓለሞች እርስበርስ አንዳቸው የሌላኛቸውን ምስል አሰይጥነው የሚያቀርቡበት የፕሮፓጋንዳ ዘመን እንደነበር በማሰብ፣ ያንን “መጪው ጊዜ” ተብሎ በአማርኛ ጭምር የተተረጎመ የትንቢት መፅሐፍ ንቄ ትቼው ነበር። አሁን ግን ኢትዮጵያ የምዕራቡ ዓለም ሸሪክና ተላላኪ፣ ቁጥር አንድ ተመፅዋች ነች። ወደ ሌሎች ዓለማት ከሚፈልሱ ኢትዮጵያውያን ይልቅ ወደምዕራቡ ዓለም የሚፈልሱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በሺህዎች እጥፍ ይልቃል። ኢትዮጵያና የተተበተበችበት ኋላቀር የብሔር-ብሔረሰብ ምናምንቴ ሥርዓት ራሱ፣ በቀጥታ በምዕራቡ ዓለም የታቀደላትና ጮቤ የሚያስረግጣቸው ሥርዓት ነው አሁን በኢትዮጵያችን የነገሠላቸው! … ታዲያ እነዚህ ሰዎች (ማለቴ ምዕራባውያን) ዛሬም እንደ ትናንቱ የሶሻሊስቷ ኢትዮጵያ ዘመን ኢትዮጵያን ወደፊት በጠላትነት የምትሰለፍባቸው፣ ከእነርሱ ይልቅ ከኢራን ጋር የምትገጥምና የምትወጋቸው አድርገው የሚያስቧትና የሚፈሯት…፣ ትንቢትና ጥንቆላቸውን የሚያዘንቡባት… ለምንድነው? (የተደጋገመ ሟርታቸው ከየት የመጣ ነው?) – ግራ ይገባኛል! እና … ምናልባት ይሄ ነገር እውነት ቢሆንስ? ብዬ እጠይቃለሁ። አባባሌ…፣ እውነት ግን የኢትዮጵያ መጨረሻ… እንዲያ ይሆን? … በተለይ እኛ ለዘመናት ራሳችንን “ጥቁር እስራኤሎች” (“Black Zions) እያልን ስንጠራና ስንፎክር…፣ እና በእስራኤል አምላክ ስም ስንምል የኖርነው ኢትዮጵያውያን…. እውነት ምን ምክንያት ተገኝቶ ነው?.. በፍፃሜው ጦርነት ከፐርሺያኖች ጋር ገጥመን እስራኤሎችን ለመውጋት የምንነሳው?? I don’t know! አንድዬ ይወቅልን!

አንድ የአፍሪካ (የጋና) ምሁር የፃፈውን ትክክለኛዎቹ እስራኤላውያን ዛሬ ራሳቸውን እስራኤሎች ነን ብለው ዓለምን ያሳመኑት እስራኤሎች ሳይሆኑ፣ ለሙሴ ሚስቱን ሲጳራን የዳሩለትና በጣና ገዳማት ፈጣሪያቸውን ሲያመልኩ የኖሩት ኢትዮጵያውያን ናቸው፣ የመፅሐፍ ቅዱሱ ትንቢት ባለቤቶች ኢትዮጵያውያን ናቸው፣ የኢትዮጵያ የቅድስና ብኩርና ከመካከለኛው ምሥራቅ በፈለቁት የዛሬዎቹ እስራኤሎች ተዘርፏል… የሚል ቴሲስ ማስነበቡን አስታውሳለሁ! እና ሳስው (የሠይጣን ጆሮው ይደፈንልንና) እኛ ኢትዮጵያውያን እውነተኞቹ እስራኤሎች ከሆንን፣ የአርማጌዶኑ መቅሰፍት የሚያርፈውም በእኛ ላይ፣ በአሜሪካ እርዳታ የምንድነውም እኛ ነን ማለት ነው!? እንዲያ ከሆነ ግን…፣ እሺ በቅዱስ መፅሐፉ በትንቢተ እዝቅኤል ከኢራን ጋር ተሰልፈው እስራኤልን ያነዷታል የተባሉት እውነተኞቹ ኢትዮጵያውያንስ ማን ናቸው ልንል ነው? ማን ነን ግን እኛ? ማነች ትክክለኛዋ እስራኤልስ? አሜሪካስ ስሟ ሳይጠቀስ እውነት ለዓለም ፍፃሜ በቅታ ትዋጋለች? (እንጃ አልመሠለኝም ፈራሁኝ!) ለዓለማችን ሠላም፣ ለሀገራችንም የበለጠ የበዛ ሠላምን ተመኘሁ! (Asefa hailu)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe