የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ የኢትዮ ቴሌኮም የ2015 በጀት አመት የስራ አፈፃፀምን በሚመለከት በዛሬው እለት በስካይ ላይት ሆቴል ማብራሪያ ሰጥተዋል
በማብራሪያው እንደተገለፀው በበጀት አመቱ ኩባንያው የገቢ ምንጮችን በማስፋት በዋናነት ከመሠረታዊ ቴሌኮም አገልግሎቶች ባሻገር ያሉ በርካታ ተቋማትና አጠቃላይ ደንበኞችን ማዕከል ያደረጉ የዲጂታል መፍትሔዎች፣ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን በማቅረብ እንዲሁም የኔትወርክና የሲስተም አቅም በማሳደግ 75.8 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ በማግኘት የእቅዱን 101% አሳክቷል፡፡
ይህ ገቢ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ23.5% ብልጫ አለው፡፡ የተገኘው ገቢ በአገልግሎት አይነት ሲታይ የድምጽ አገልግሎት 43.7% ድርሻ ሲኖረው ዳታና ኢንተርኔት 26.6%፣ ዓለም አቀፍ ገቢ 9%፣ እሴት የሚጨምሩ አገልግሎቶች 6.9%፣ የቴሌኮም መጠቀሚያ መሣሪያዎች (ቀፎ፣ ዶንግል፣ ሞደም) 4.7% እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶች 7,2% ድርሻ አላቸው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በበጀት አመቱ የሞባይል ኔትዎርክ እና የብሮድባንድ ኔትዎርክ ሽፋንን ማሳደግ መቻሉም ተገልጿል፡፡
በበጀት አመቱ የውጭ ምንዛሬ ከሚያስገኙ አገልግሎቶች የተገኘው ገቢ 164 ነጥብ 1 ሚሊየን ዶላር መሆኑንም ፍሬህይወት ታምሩ ተናግረዋል፡፡በተጨማሪም በበጀት አመቱ 264 ከተሞች የሞባይል የ4ጂ አገልግሎት ማግኘት መቻሉም ተገልጿል፡፡
በበጀት አመቱ የአገልግሎቶቻችን ተጠቃሚ ደንበኞች ብዛት 72 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን አፈፃፀሙ ካለፈው በጀት ማጠናቀቂያ ከነበረበት ጋር ሲነጻጸር የ8% እድገት፣ እንዲሁም ከእቅድ አንጻር የ98% አፈጻጸም ተመዝግቧል፡፡

etio telecom

በአገልግሎት አይነት ሲታይ የሞባይል ድምፅ ደንበኞች ብዛት 69.5 ሚሊዮን፣ የመደበኛ ብሮድባንድ (Fixed Broadband) 618.3 ሺህ፣ የመደበኛ ስልክ ደንበኞች 853.6 ሺህ እንዲሁም የዳታና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች 33.9 ሚሊዮን ናቸው፡፡ የቴሌኮም ስርጸት (teledensity) መጠን 66.8% ሆኗል፡፡ ዓለም ላይ ካሉ 774 ኦፕሬተሮች መካከል በሞባይል ደንበኛ ቁጥር በአፍሪካ 2ኛ ደረጃ የያዘ ሲሆን በዓለም 21ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
በማብራሪያው እንደተገለጸው በሰሜኑ የሀገራችን ክፍልና በተለያዩ አካባቢዎች ከጸጥታ ጋር በተገናኘ ተቋርጦ የነበረውን አገልግሎት ለማስጀመር የሚያስችሉ የተለያዩ የቴሌኮም መሳሪያዎች፣ የኮመርሻልና ለአገልግሎት ማዕከላት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ከተለያዩ የኩባንያችን ጽ/ቤቶች በማሰባሰብ በአጭር ጊዜ ውስጥ አገልግሎቱን ማስቀጠል ተችሏል፡፡ በዚህም በ186 ከተሞችና ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ 943 የሞባይል ጣቢያዎች እንዲሁም 1,886 ኪ.ሜ የፋይበር መስመር በመጠገንና መልሶ በማቋቋም አገልግሎት መስጠት ተችሏል፡፡
በ20 ከተሞች የሚገኙ 22 የኩባንያችን የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት አስፈላጊውን ጥገና በማድረግና የተጓደሉ መሳሪያዎችን በማሟላት ወደ አገልግሎት መመለስ የተቻለ ሲሆን በ86 ከተሞችና ወረዳዎች የሚገኙ 38 የፋይናንስ ተቋማት የብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት በአፋጣኝ መልሶ በማስቀጠል አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ተችሏል፡፡

