የ5 ጂ የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት በይፋ ተጀመረ! ኢትዮ ቴሌኮም የአምስተኛው ትውልድ (5 ጂ) የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት በይፋ አስጀመረ።ኢትዮ ቴሌኮም የ5 ጂ አገልግሎትን በአዲስ አበባ በተለያዩ አካቢዎች በሚገኙ በ145 ስፍራዎች ማስጀመሩን በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል።
የ5 ጂ የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት እስከ 10 ጊጋባይት በሰከንድ የሚደርስ ከፍተኛ ፍጥነት ያለው መሆኑ ተመላክቷል።የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ በይፋ ማድረጊያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የ5 ጂ አገልግሎት ስራ ላይ መዋሉ የማህበረሰባችንን ህይወት የሚያቀሉ ዲጂታል መፍትሄዎችን በቀላሉ በማቅረብ ተሞክሯቸውን የሚያሻሽል መሆኑን ተናግረዋል።ደንበኞች የ5 ጂ አገልግሎትን ለመጠቀም የሚያስችሉ መሳሪያዎችና ቀፎዎች ሊኖራቸው እንደሚገባም ተመላክቷል።
ኢትዮ ቴሌኮም የ5ኛውን ትውልድ (5G) የሞባይል ኔትወርክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሞከው በአዲስ አበባ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ነበር። በቀጣይም በሙከራ ደረጃ በአዳማ ከተማ አገልግሎቱን ሲሰጥ ቆይቷል።

ይህ የ5G ኔትዎርክ አገልግሎት በአዲስ አበባ ተደራሽነቱን አስፍቶ ለተጠቃሚዎች መቅረቡን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬህይወት ታምሩ ዛሬ በነበረው ይፋዊ የማብሰሪያ መድረክ ላይ ተናግረዋል።
እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገለጻ በኢትዮጵያ ይህንን አገልግሎት በአዲስ አበባ 145 ሳይቶች ላይ የ5G ኔትዎርክ ማስፋፊያ የተደረገ ሲሆን 630 ሺ ደንበኞቹ ይህንን አገልግሎት ለመጠቀም የሚያስችል ቀፎ (Device) መኖሩን አስታውቀዋል።
ይህ አገልግሎት ከተዘረጋባቸው ቦታዎች መካከል ከመስቀል አደባባይ እስከ ቦሌ ኤርፖርት፤ ከመስቀል አደባባይ መገናኛ CMC እንዲሁም ወደ ሰሚት የሚወስደው መንገድ፤ ከመስቀል አራት ኪሎና ስድስት ኪሎ ድረስ፤ ከመስቀል አደባባይ ሜክሲኮ ሳር ቤት እንዲሁም ልደታ ከመስቀል አደባባይ ለገሀር ቸርቸል ጎዳና ይህ መሰረተ ልማት የተዘረጋላቸው አከባቢዎች ናቸው ተብሏል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ በመግለጫቸው ተቋሙ በቀን በአማካይ ወደ 2,087 GB የዳታ ትራፊክ መኖሩን የገለጹ ሲሆን ከዚህ ውስጥም የ4G አገልግሎቱ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ ጠቁመዋል።
በአለማችን ወደ 110 ሀገረት በአፍሪካ ደግሞ 16 ሀገራት ይህንን አገልግሎት የጀመሩ ሲሆን አሁን ላይ 1.3 ቢሊዮን ተጠቃሚዎችን የ5G ኔትዎርክ ተጠቃሚ መሆናቸው በመድረኩ ተገልጿል።

