በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎትና አጋሮቹ በተካሄደው አገር አቀፍ የዴሞግራፊና ጤና ዳሰሳ ጥናት፤ 55 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ባል ሚስቱን ለመምታት የሚያስችሉ አሳማኝ ምክንያቶች አሉ ብለው እንደሚያምኑ ይፋ ሆነ።
በጥናቱ ከተሳተፉት መካከል ይህንን አመለካከት የሚጋሩት የወንዶች ቁጥር 39 በመቶ ሲሆን፣ አብዛኞቹ ምላሽ ሰጪዎች ለምታ በቂ ምክንያት አድርገው የጠቀሱት “ልጆችን ቸል ማለት” የሚለውን ነው።
📌የለውጥ ሂደት፡ ድብደባውን የሚደግፉ ሴቶች ቁጥር ከ25 ዓመት በፊት ከነበረበት 85 በመቶ አሁን ወደ 55 በመቶ ቢቀንስም፤ የወንዶች ድርሻ ግን ከ10 ዓመት በፊት ከነበረበት 28 በመቶ ወደ 39 በመቶ አድጓል።
📌የክልልና የትምህርት ልዩነት፡ በሲዳማ ክልል 74% ሴቶች ድብደባውን ሲደግፉ፣ በሶማሌ ክልል ግን 23% ብቻ ነው። በተጨማሪም ያልተማሩ ሴቶች ድብደባውን የመደገፍ እድላቸው (63%) ከተማሩት (29%) በእጅጉ የላቀ ሆኖ ተግኝቷል።
በጥናቱ መሠረት ባል ወይም አጋር ካላቸው ሴቶች 30 በመቶ ያህሉ ጥቃት የደረሰባቸው ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 58 በመቶ የሚሆኑት ምንም ዓይነት እገዛ አልጠየቁም። የሴቶች መብት ተሟጋቾች ይህንን ጎጂ አመለካከት ለመቀየር የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅም ማሳደግና ሰፊ የግንዛቤ ሥራ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

