በዋሽንግተን የእስራኤል አምባሳደር የሂኤል ሌይተር ሄዝቦላህ የጦር መሳሪያ ታጥቆ እስካለና የእስራኤልን ሰላማዊ ዜጎች ስጋት ላይ መጣሉን እስከቀጠለ ድረስ የሀገሪቱ መከላከያ ሠራዊት በሊባኖስ ውስጥ ባቋቋመው የደህንነት ቀጠና ውስጥ መቆየቱን ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ከቤሩት ጋር በሚደረገው ድርድር የእስራኤልን ቡድን እየመሩ ያሉት አምባሳደሩ የዚህ ስምምነት ዓላማ ኢራን እና ሄዝቦላህን ማስወጣት ነው ብለዋል፡፡
ኢራን በሊባኖስ ውስጥ ምንም አይነት ህጋዊ ሚና እንደሌላትና ለእስራኤል ደህንነት ሲባልም ሆነ ለሊባኖስ ሉዓላዊነት መወገድ አለባት በማለት ተናግረዋል፡፡
አምባሳደሩ አክለውም ሄዝቦላህ ትጥቅ በፈታ ማግስት እኛም ሊባኖስን ለቀን መውጣት እንችላለን ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል የእስራኤል ጦር በጋዛ የሐማስ ጦር አዛዥ መገደሉን አስታወቀ፡፡
አዛዡ በጋዛ በእስራኤል ጦር ጥቃት በማድረስ ረገድ ከፍተኛ ተሳትፎ የነበረው እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ጦሩ በማዕከላዊ ጋዛ በሰነዘረው ጥቃት የቃሳም ብርጌድ ክፍልን በበላይነት የሚመራውን የሻለቃ መኮንን ዑመር አህመድ አቡ ቃሰምን መግደሉን አስታውቋል፡፡
ጥቃቱ የተፈጸመው በጦር መሪው የቤተሰቦች መኖሪያ አፓርታማ ላይ ሲሆን፤በጥቃቱም ባለቤቱን ጨምሮ የስድስት ዓመት ሴት ልጁ ተገድለዋል፡፡
የእስራኤል ጦር አቡ ቃሰም በጦርነቱ በጋዛ ሰርጥ ውስጥ በእስራኤል ወታደሮች ላይ በሚሰነዘሩ ጥቃቶች ላይ በቀጥታ ይሳተፍ እንደነበር ገልጻል፡፡
በጋዛ ካለፈው ዓመት ጥቅምት ጀምሮ የተኩስ አቁም ስምምነት የተደረሰ ቢሆንም፤ባለፉት ሁለት ቀናት ብቻ እስራኤል በፈጸመችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 12 ሰዎች መገደላቸው ታውቋል፡፡//

