ኦነግ  እጩዎችን እንዲያስመዘግብ ድጋሚ እድል ሊሰጠው  እንደሚችል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍንጭ ሰጡ

  • ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ሊፈተኑ ነው፤

    በሁለቱ የኦነግ አመራሮች መሀከል የተፈጠረውን አለመግባባት መነሻ በማድረግ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሂድ ከምርጫ ቦርድ መመሪያ ተሰጥቶአቸው የነበረው ሁለቱ የኦነግ አመራሮች በጭቅጭቅ ጠቅላላ ጉባኤ ሳያካሂዱ የእጩዎች የምርጫ ምዝገባ ቀን ማለፉ ይታወሳል፡፡

    በእነ አቶ ቀጀላ መርዳሳ  የሚመራው ኦነግ ባለፈው ሳምንት የምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፖርቲዎች የእጩዎች ማስመዝገቢያ ቀናት ከተጠናቀቀ በኋላ ጠቅላላ ጉባኤ አድርጌያለሁ ማለቱን ተከትሎ በምርጫው ለመሳተፍ ጥያቄ ማቅረቡ መዘገቡ ይታወሳል፤

    በምርጫ ህጉ መሠረት የእጩዎች ማስመዝገቢያ ቀናት ከተጠናቀቁ በኋላ እጩዎችን የማስመዝገብ ጥያቄ ተቀባይነት የሌለው ቢሆንም ጠቅላላ ጉባኤ ያደረገው ኦነግ ግን በልዩ ሁኔታ ምርጫ ቦርድ እጩዎቹን አስመዝግቦ እንዲወዳደር መንግስት ፍላጎት እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ተናግረዋል፡፡

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለፁት  በተለይ በኦሮሚያ  አባላቶች ስለታሰሩብኝና ብሔራዊ መግባባት ሳይኖር ወደ ምርጫ አልገባም ያለውን ኢፌኮን ጨምሮ ሌሎችም ፖርቲዎች በምርጫው እንዲሳተፉ ራሳቸው ጭምር ጥያቄ ማቅረባቸውን ጠቅሰው  ምክንያት በመደርደር ራስን ከምርጫው ማግለል ለዲሞክራሲያዊ ግንባታ ያለው ጠቀሜታ እምብዛም ነው ብለዋል፤

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት በሰጡት ማብራሪያ ኦነግ ለምርጫ ቦርድ  የእጩዎች የምዝገባ ቀን ካለፈ በኋላ  ጥያቄ ቢያቀርብም ምርጫ ቦርድ በልዩ ሁኔታ ምላሽ እንደሚሰጠው ተስፋ አደርጋለሁ በማለት የወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ነጻና ገለልተኛነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

    ወ/ሪት ብርቱካን በህግና በህግ አግባብ ብቻ በመመራት በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ሊባል የሚችል ምርጫ ለመምራት መዘጋጀታቸውን በተለያየ ጊዜ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ምርጫ ቦርድ ኦነግን ወደ ምርጫ የሚገባበትን ዕድል ህጉን ጥሶ ይፈቅድለታል ወይስ የሚለው በቀጣይ ቀናት የሚወሰን ይሆናል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe