“ከሀዲው የትህነግ ቡድን የፈጸመውን ተግባር በሀሳብ፣ በጽሁፍ፣ በፕሮፖጋንዳ፣ በማህበራዊ ሚዲያም ይሁን በሌላ መንገድ መደገፍ ወንጀል ነው”

“ከሀዲው የትህነግ ቡድን የፈጸመውን ተግባር በሀሳብ፣ በጽሁፍ፣ በፕሮፖጋንዳ፣ በማህበራዊ ሚዲያም ይሁን በሌላ መንገድ መደገፍ ወንጀል ነው”
– አቶ ውብሸት ሙላት የህግ ባለሙያ
(ኢ ፕ ድ)ዘራፊው የትህነግ ቡድን በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ የፈጸመውን የአገር ክህደት ተግባርንም ሆነ በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸመውን ጭፍጨፋ በሀሳብም፣ በጽሁፍም፣ በፕሮፖጋንዳም፣ በማህበራዊ ሚዲያም ይሁን በሌላ መንገድ መደገፍ ወንጀል ነው፤ ከሞራል አንጻርም ነውር ነው” ሲሉ የሕግ ባለሙያው አቶ ውብሸት ሙላት ገለጹ፡፡
የህግ ባለሙያው አቶ ውብሸት በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ዘራፊው የትህነግ ቡድን በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ የፈጸመው ጥቃት የአገር ክህደት፣ ህገመንግስትን የማፍረስና የሽብር ተግባር ሲሆን፤ በዓለማቀፍ ህጎች፣ ስምምነቶችና ፕሮቶኮሎች አንጻር የሚታዩ ናቸው፡፡
በተመሳሳይ በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋም በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ሲሆን፤ ሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ደግሞ በይርጋም አይታገድም፤ ይቅርታም አይሰጠውም፤ ምህረትም አይደረግለትም፡፡ በመሆኑም ይሄንን የትህነግ ቡድን የፈጸመውን ተግባር መደገፍ በራሱ ወንጀል ነው፡ ብለዋል፤አቶ ውብሸት።
እንደ ህግ ባለሙያው ገለጻ፤ በዚህ መልኩ ዘራፊው የትህነግ ቡድን የፈጸመውን ወንጀል በሀሳብም ይሁን፣ በጽሁፍም ይሁን፣ በፕሮፖጋንዳም ይሁን፣ በማህበራዊ ሚዲያም ይሁን በሌላ መንገድ ይሄንን የወንጀል ድርጊት መደገፍ ወንጀል ነው፡፡ በመሆኑም ህብረተሰቡም ሆነ ሌሎች አካላት ከዚህ አይነት ድርጊት ሊቆጠቡ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ይሄን ማድረግ አንድም ወንጀልን ማበረታታት ነው፤ ሁለተኛም የወንጀል ድርጊቱን መደገፍ ነው፡፡
ይሄን ማድረግ ደግሞ በህግም ክልክል ነው፤ ከሞራልም አንጻር ተገቢ አይደለም፡፡ መንግስትም የህግ ማስከበር እርምጃውን በሚወስድበት ሂደት በተቻለ መጠን ንጹሃን ዜጎች (ሲቪሊያን) እንዳይጎዱ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ማከናወን አለበት፡፡ ሂደቱንም በተቻለ ፍጥነት፣ በታለመና በታቀደ ሁኔታ በወንጀሉ የተሳተፉትን ወደ ፍትህ የማምጣቱ ስራ ላይም ትኩረት ማድረግ ይኖርበታል፤ ሲሉ አቶ ውብሸት አሳስበዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe