ከሦስት ዩኒቨርሲቲዎች በሱስ ምክኒያት የተባረረው እና ፊዚክስ የሚያስጠናው ግለሰብ ጉዳይ እጅጉን መነጋገሪያ ሆኗል፡፡
በኦን ላይን ፊዚክስ በማስተማር ዝነኛ የሆነው ዳኛቸው አሰፋ ወይም በተማሪዎቹ አጠራር መምህር ዳኒ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ትምህርት መቀበል አይችሉም ከሚባሉ ልጆች እንደነበር ይናገራል፡፡
ዳኛቸው ጉበዝ ተማሪ ለመሆን በወቅቱ ጎበዝ ተማሪዎች ከነበሩ ጓደኞቹ ምክር ተቀብሎ እርሱም ጎበዝ ተማሪ ለመሆን ከአሳ ዘይት መጠጣት፡እስከ ሜዲቴት ማድረግ እና ቴኳንዷ መስራት ሁሉንም እንደሞከረ ግን ምንም ለውጥ እንዳላመጣም ያስታውሳል፡፡
ከጓደኞቹ ኮርጆ 96 ፕርሰንታይል ያመጣው የ8ኛ ክፍል ውጤት ግን የህይወቱን ምዕራፍ ለውጦታል፡፡ በውጤቱ በጣም የተደሰቱትን አባቱን ላለማሳፈር እና የመጣው ውጤትም በኩረጃ እንዳልሆነ ለማሳየት ብዬ ማጥናት ጀመርኩ ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ ጎበዝ ተማሪ መሆን ቻልኩ ይላል፡፡
ዳኛቸው ሻምበል ውልደት እና እድገቱ በድሬዳዋ ሲሆን እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርቱን ያጠናቀቀውም በዚያው ነው፡፡
በ2007 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና 515 በማምጣት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲን ተቀላቀለ፡፡ በዩኒቨርሲቲው የሜካኒካል ምህንድስና ትምህርት ክፍል ለ1 ዓመት ከ6 ወር ቢማርም በሱስ ምክኒያት ትምህርቱን ማጠናቀቅ ሳይችል ቀረ፡፡
ወደ ቻይና የመሄድ እድል ያገኘው ዳኛቸው በዚያም በሱሱ ምክኒያት ትምህርቱን መከታተል አቃተው፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ቻይና ሐንዡ የምትባል ከተማ የኮምፒውተር ትምህርት ለመማር ቢሄድም አሁንም ትምህርቱን መቀጠል አልቻለም፡፡
በዚህም ምክኒያት በቻይና ፖሊስ በቁጥጥር ስር ለቀናት ከቆየ በኋላ ወደ ኢትዮጽያ እንዲመለስ መደረጉን ያስታውሳል፡፡
ከዚያም በአዲስ አበባ እና በቢሾፍቱ ጎዳናዎች ላይ እስከመኖርም ደርሷል፡፡ በአንድ አጋጣሚ ከቢሾፍቱ ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ የተዋወቃት ሴት የህይወቱን ምዕራፍ እንዲለወጥ እንዳደረገችው ያስታውሳል፡፡ ይች ሴት ዛሬ ባለቤቱ ነች፡፡
ከእርሷ ጋር መኖር ከጀመርኩ በኋላ ከሱስ መራቅ ጀመርኩ፡ ወደ ፈጣሪየ ተጠጋሁ የሚለው ዳኛቸው በኮሮና ወቅት የስምተኛ ክፍል ተማሪዎችን ማስጠናት እንደጀመረ በኋላም መምህር እስኪመጣ ተብሎ በመምህርነት ማስተማር እንደጀመረ ይናገራል፡፡
በዚያች አጋጣሚ የተጀመረችው የማስተማር ሕይወት ዛሬ መምህር ዳኒ የሚለውን ስም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ እንዲጎላ አድርጎት ቀጥሏል፡፡
በዚህ ወቅት በማህበራዊ ሚዲያ የፊዚክስ ትምህርትን በተለዬ የማስተማር ዘዴ በማስተማር መምህር ዳኒ የሚለው ስምም ጎልቶ እንዲወጣ አድርጎታል፡፡//

