የፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ ከእስራኤል ጋር ሁሉን አቀፍ የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገለፁ። አባስ ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት በፃፉት ደብዳቤ በእስራኤል እና በኢራን መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ትራምፕ ላደረጉት የተሳካ ጥረት ያላቸውን ጥልቅ ምስጋና እና አድናቆት ገልፀዋል ሲል ኦፊሴላዊው የዜና ወኪል ዋፋ ዘግቧል።
በኢራን እና በእስራኤል መካከል የተካሄደውን የተኩስ አቁም ስምምነት ቀውሶች ለማርገብ አስፈላጊ እና ጠቃሚ ርምጃ ሲሆን ይህም በአካባቢው ደህንነት እና መረጋጋት ላይ በጎ ተጽእኖ ይኖረዋል ሲሉ አሞከሽተዋል። እስራኤልና ኢራን ከ12 ቀናት ውጊያ በኋላ በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አማካኝነት ግጭታቸውን ለማቆም የተኩስ አቁም ማድረጋቸው ይታወሳል። በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግና ፍልስጤማውያን፣ እስራኤላውያን መካከል ሁሉን አቀፍ ሰላም ለማምጣት ትራምፕ ለሚያደርጉት ወሳኝ ጥረት አድናቆት ችረዋል።
አባስ ከትራምፕ፣ ከሳውዲ አረቢያ እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በቀጠናውና በሀገራቸው ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ተባብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አመልክተዋል። አባስ ለትራምፕ በፃፉት ደብዳቤ ላይ እንደገለፁት፤ ከእርስዎ ጋር የማይቻል የሚመስለውን ነገር ማሳካት እንችላለን ብለዋል። እውቅና ያላት፣ ነፃ፣ ሉዓላዊ እና አስተማማኝ ፍልስጤምን ብሎም እውቅና ያላትና ደህንነቷ የተጠበቀ ሰላም፣ ብልጽግና የሰፈነባት እስራኤልን ብሎም የተረጋጋ ቀጠና መፍጠር እንችላለን ማለታቸውን ሚድል ኢስት ሞኒተርና አናዶሉ ዘግበዋል።

