” ከደመወዝና ሰራተኞች ጥቅማጥቅም ባሻገር የዚህ አንጋፋ ተቋም ህልዉና አደጋ ዉስጥ መሆን ያሳስበናል ” – የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ሠራተኞች

የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ከቀድሞዉ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መፍረስ በኋላ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዉ እየተዳከመ መጥቶ አሁን ላይ ፦
– የሰራተኞች ደመወዝ ፣- የደሞዝ ማሻሻያ (Back Payment)፣- የደረጃ ዕድገትና ሌሎችም ጥቅማጥቅሞች መክፈል አለመቻልን ጨምሮ የመፍረስ አደጋ እንደተጋረጠበት የተቋሙ ሠራተኞች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
ስማቸዉ እንዲገለፅ ያልፈለጉ አንድ የድርጅቱ አንጋፋ ጋዜጠኛ ፥ ” ተቋሙ አሁን ላይ የተጋረጠበት አደጋ በወር ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም አለመኖር ብቻ የሚመዘን ሳይሆን የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ድምፅ በመሆን ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በልማት፣ መልካም አስተዳደደርና በደሞክራሲ ግንባታ ረገድ ጉልህ አበርክቶ ያለዉ ከመሆኑም በላይ ለሀገራችን የሚዲያዉ ኢንዱስትራ በርካታ ባለሙያዎችን ያፈራ አንጋፋ ተቋም እንደመሆኑ በዚህ ልክ አስታዋሽ ያጣ መሆን አልነበረበትም ” ብለዋል።
ሌሎች ሰራተኞች በበኩላቸው ” የደመወዝና ስራ ማስኬጃ በጀት ከአራቱ ክልሎች እየተዋጣለት እስካሁን የቆየዉ ድርጅቱ ባለቤት አልባ፣ ተቆርቋሪ እና ጠያቂ ያጣ ስለመሆኑ ማሳያ የሚሆነዉ እስካሁንም ዋና ስራ አስፈፃሚዉን ጨምሮ የተቋሙ አመራሮች በዉክልና ለረጅም ጊዜ የቆዩ መሆናቸው ነው ” ብለዋል።
” ግምገማ ኦዲትና የቅርብ ክትትል የሚያደርግ አካልም ባለመኖሩ ከደመወዝና ሰራተኞች ጥቅማጥቅም ባሻገር የዚህ አንጋፋ ተቋም ህልዉና አደጋ ዉስጥ እንደሆነ ይሰማናል ” ሲሉ ገልጸዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ ያነጋገራቸው ከዚህ ቀደም በተቋሙ የሰሩ በአሁኑ ወቅትም በሀገራችን ትልልቅ የሚዲያ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎች ” ከ48 ቋንቋዎች በላይ ወደ አድማጭ ተመልካቾቹ የሚደርሰዉ ይህ አንጋፋ ተቋም በዚህ ልክ ትኩረት መነፈጉና ለበርካቶች ድምፅ መሆን የቻሉ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ባለሙያዎች በዚህ ልክ ትኩረት ተነፍገዉ ማየት በጣም ያሳዝናል ” ሲሉ ሃሳባቸዉን ገልፀዋል።
” የፌደራል መንግስት ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትም ለዚህ ተቋም መጠናከር የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል” ሲሉ ባለሙያዎቹ አክለዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe