ካፒቴን ኢብራሂም ትራውሬ ዳግማዊ ቶማስ ሳንካራ?

(በአብርሃም መኻንንት) ካፒቴን ኢብራሂም ትራውሬ፡ኮሎኔል አስሚ ጎይታ ጀነራል አብዱር ሀማ ኒቲያሚ እነዚህ ስሞች ከወደ ምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የተዋወቅናቸው እና መላው ዓለመም አጀንዳ አድርጓቸው የዘለቁ ናቸው፡፡ ማሊ፡ኒጀር፡ቡርኪናፋሶ ደግሞ ሀገራቱ ናቸው፡፡

እነዚሁ ምዕራብ አፍሪካዊ ሀገራት በ 3 ዓመት ጊዜ ብቻ ከ 5 በላይ ወታደራዊ መፈንቀለ መንግስትን ያስተናገዱ ናቸው፡፡

እናም ከ2021 እስከ 2023 ባሉት ጊዚያት ሦስት አብዮተኞች ሦስት ወታደራዊ ማዕረግ ያላቸው ወጣት መሪዎች ወደ መንበሩ ዘልቀው ቀጥለዋል፡፡

ከሦስቱም ውስጥ ኢብራሂም ትራውሬ የሚለው ስም ገኖ ይሰማል፡፡ ይህንን ሰው ዳግማዊ ቶማስ ሳንካራ እያሉ የሚጠሩት ብዙዎች ናቸው፡፡

ብዙ የሚያመሳስሏቸው ነገሮችም አሏቸው፡፡ ቶማስ ሳንካራ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ነበር ወደስልጣን የመጣው ልክ እንደ ትራውሬ፡፡ እድሜውም 34 ነበር ልክ እንደ ትራውሬ፡፡

ትራውሬ ከቶማስ ሳንካራ የወሰዳቸው የፓን አፍሪካኒስት ሀሳቦቸም እንዳሉት ብዙዎች ይገልጻሉ፡፡ እነዚህንና ሌሎችን ሃሳቦች በመገጣጠም ነው ዳግማዊ ቶማስ ሳንካራ ሲሉ የሚጠሩት፡፡

እርግጥ ሦስቱም አብዮተኞች ነጻነትን የተራቡ፡የእጅ አዙር አስተዳደርን ፈጽመው የጠሉ፡ሀገራቸውን ውድ ማዕድናትን ለሌሎች ሀገራት የሚቸበችቡ የይስሙላ መሪዎቻቸውንም የተጠየፉ ናቸው፡፡

እናም ሦስቱም አብዮተኞች የቀድሞ የቀኝ ገዢ የነበረችው ፈረሳይ ጦሯን ከየሀገራቱ እንድታስወጣ በማድረግ ነበር የለወጥ ጉዟቸውን አንድ ብለው የጀመሩት፡፡

የአሜሪካንም ጦር በተመሳሳይ፡፡ ኢብራሂም ትራውሬ የወርቅ ማጣሪያ ፋብሪካዎችን፡የቲማቲም ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን፡የባቡር መንገድ ዝርጋታዎችን እና የከተማ ቤት ልማት ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር ጊዜ የወሰደበት መሪ አይደለም፡፡

ቡርኪናዎች በኢብራሂም ትራውሬ አስተዳደር ደስተኞች እንደሆኑ በየአደባባዮች በመውጣት ገልጸውላቸዋል፡፡ በውጭ ሀገር ያሉ ቡርኪናቢ ዳያስፖራዎችም ብቻ ፈረንሳዮችን ከሀገራችን አስወጣልን እንጂ እኛም ጓዛችንን ጠቅልለን ወደቤታችን ገቢዎች ነን ሲሉም አድምጠናል፡፡

የጅኦሎጂ ምሩቁ፡ካፒቴኑ እና ፕሬዜዳንቱ ትራውሬ ብዙ የማይታመኑ ለውጦችን ለቡርኪናዎች እያበረከቱ ቀጥለዋል፡፡ በርሃብ ይቀጡ የነበሩ ዜጎቹን የስራ እድሎችን በመፍጠር በልተው እንዲያድሩ ለማድረግ እየጣራ ነው፡፡ ሰሪ፤ፈጣሪ የነበሩ የውጭ

ሃይሎችን ጠራርጎ አስወጥቶ ፍጹም ሉዓላዊ ሀገር እንድትሆን የማድረግ ህልሙን ተያይዞታል፡፡

አሁን አንዳንዶች እንዲህ ይሰጋሉ ትራውሬ አነሳሱ እንደ ሳንካራ እንደሆነው ሁሉ ፍጻሜውም እንደርሱ እንዳይሆን እያሉ፡፡

እንዴት ካሉ ሳንካራ በምዕራቡ እና ቀኝ ገዥ በሆኑ ሀገራት አይወደድም ነበር፡፡ ትራውሬም እንደዛው እናም ካልተወደዱ ደግሞ እንዲገደሉ ሊደረጉ ይችላሉ፡፡ ይህ ግን ለትራውሬ ጉዳዩ የሆነ አይመስልም፡፡ እንዲህ ለሚሉት ቡርኪናቢዎች ደግሞ የትራውሬ መልስ አንድ ነው፡፡

ስለእናተ እና ስለሀገሬ መራራውንም ሞት እጎነጨዋለሁ ነው፡፡ ይህ የትራውሬ ቃልና ድርጊቱ የሚጣጣም በመሆኑ ቡርኪናቢዎች ልብባቸውን ለእርሱ ለመስጠት ሲከብዳቸው አልታየም፡፡

ትራውሬን ከስልጣን የማንሳት ሙከራዎች ከዚህ በፊት ተሞክረው እንደነበር ሰምተናል፡፡

አሁን ወደ ቀኝ ግዛት ዘመን ሊመልሱን ከሚፈልጉ ሀገራት ጋር ነው እየተዋጋን ያለነው ደግሞ እርግጠኛ ሆኜ ልንገራችሁ እናሸንፋቸዋለን እያየን ያለነውም እርሱን ነው፡፡ እናም ከጎናችን ተሰለፉ እያለ ጥሪ እያቀረበ ነው አብዮተኛው መሪ፡፡

በእርግጥ ትራውሬ ወደ ስልጣን እንደመጣ በብዙዎች ዘንድ ወጣት መሆኑና ልምድ ያለው ሰው ባለመሆኑ የመሪነት ብቃቱ ጥርጣሬ ውስጥ እንዲወድቅ አድርጎት እንደነበር ይታወሳል፡፡

ነገር ግን የተፈራው ሁሉ ሳይሆን ሰውየው በሁለት ዓመት ብቻ የሀገሪቱን የወደፊት እድል የሚወስኑ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን መስራት ጀመረ፡፡

ከእነዚህም ውስጥ በ8ሚሊየን ዶላር የተገነባው የቲማቲም ማቀነባበሪያ ፋብሪካ እንዲሁም በሚሊየን ዶላሮች ወጭ የተገነባው የወርቅ ማጣሪያ ፋብሪካን ጨምሮ የ55 ሆስፒታሎች ግንባታ ጅማሮ እንዲሁም የ50ሺ የከተማ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ መጀመር ሰውየው ተዓምር እየፈጠረ ስለመሆኑ ማሳያዎች ናቸው፡፡ እናም ትራውሬ ጀግና፡አብዮተኛ የሚሉ የሙገሳ ቃላቶች ከዚህም ከዚያም እየጎረፉለት ቀጥሏል፡፡

ማንም የማይዘውራትን፡ማዕድኗንንም የማያሸሹባትን ነጻ እና ፍጹም ሉዓላዊት የሆነች ሀገርን ለመፍጠር ነው ህልሜ ለሱም ነው እየሰራሁ ያለሁት ይላል ትራውሬ፡፡

የማሊው አስሚምሆነ የኒጀሩአ አብዱራሃማ የትራውሬን ህልም ተጋሪ ሆነው በተመሳሳይ መስመር ሀገራቸውን ለማስጓዝ በመንገድ ላይ ናቸው፡፡ የችግራችን ምንጭ ነው ብለው ከለዩት የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የትብብር ማዕቀፍ ከሆነው ኢኮዋስም በይፋ ወጥተው የራሳቸውን አዲስ የትብብር ጥምረት መስርተዋል፡፡ ኢኮዋስ የሀገራችንን ማዕድናት አሳልፎ

በመስጠት፡ቀጠናውን በእስላማዊ ታጣቂ ሃይሎች እንዲናጥ እና ድህነት እንዲስፋፋ ከማድረግ ውጭ ያመጣው ለውጥ የለምና መለየትን መርጠናል ብለው ነው የተለዩት፡፡

ኢኮዋስ ሀገራቱ ከጥምረቱ እንዳይወጡና ሃሳባቸውንም እንዲያጤኑት እያለ ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም ሳይሳካላት ቀርቶ እነ ትራውሬ፡አስሚ ጎይታ እና እነ አብዱር ሃማ የሳህል ሀገራት ጥምረትን መስርተው የራሳቸውንም ፓስፖርት እና ባንዲራ ይፋ አድርገው ቀጥለዋል፡፡ በቅርቡም የጋራ መገበያያ ገንዘብ ይፋ እንደሚያደርጉ በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡

5000ሺ ያህል አባላት ያሉትንም የጋራ ጦር መስርተው የቀጠናው ፈተና የሆነውን የታጣቂዎችን ስጋት ለመቀልበስ እየሰሩ ስለመሆናቸው እየተገለጸ ነው፡፡

ወርቅ፡ዩራኒየም እና የጥጥ ምርት ሀገራቱ የታደሉት ሃብቶች ቢሆንም ከዚህ ቀደም ወደ ፓሪስ ሰዎች ካዝና እንጂ ወደ ቡርኪናዎች፡ወደ ማሊዎች እና ኒጀር ዜጎች ካዝናዎች አይገባም ነበር፡፡

እናም ሰዎቹ ቢዘህ ቁጭት ነውና ወደመንበሩ የመጡት አሁን አንዳች የሚያስቆመን ምድራዊ ሃይል አይኖርም በሚል ቀጠናውን እና ሀገራቱን ለመለወጥ እየተጉ ነው፡፡

አፍሪካ ከዚህ ቀደምም አብዮተኛ መሪዎችን አይታ ታውቃለች፡፡ ነገር ግን እነዚህ አብዮተኛ መሪዎች ህልማቸውን በሙሉ እውን አድርገው አላለፉም፡፡

ምክኒያቱም ጥቅማችንን ነክተዋል፤የምንላቸውንም አያደርጉም በሚሏቸው ሀገራትና መሪዎች እንዲነሱ ሆነዋልናነው፡፡

አሁን ኒጀር፡ማሊ እና ቡርኪናፋሶ ዘመናትን አለቃ ሆና ስታስተዳድራቸው ከነበረችው ፈረንሳይ ነጻ መሆናችንን አረጋገጠናል እያሉ ነው፡፡

ሩሲያ ደግሞ አዲሷ የጦር አጋር የሆች ትመስላለች፡፡ እነዚሁ የሳህል ሀገራት ጥምረት ከሩሲያው የጦር ካምፓኒ ቫግነር ጋር በወታደራዊ ጉዳዮች ዙሪያ አብረው ለመስራት ስምምነት ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡ አንዳንዶች ይህንን ሁኔታ ተረኛዋ የማዕድን ዘራፊና የእጅ አዙር መሪ ሩሲያ እንዳትሆን እያሉ ስጋት ቢጤ ሲያነሱ ይሰማሉ፡፡

እነ ኢብራሂም ትራውሬ ግን ያዘመን ተመልሶ ላይመጣ እኛም ተመልሰን ላንተኛ አሁን በስራ ላይ ነን ብቻ እንተባበር እንጂ በዚህስ ሃሳብ እንዳይገባችሁ እያሉ ነው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe