ዋሽንግተን ሄልዝ ኬር የተመሰረተበትን 10ኛ ዓመት በድምቀት አከበረ

የተመሰረተበትን 10ኛ ዓመት ትላንት ምሽት በሃያት ሪኤጀንሲ ሆቴል ያከበረው ዋሽንግተን ሄልዝ ኬር ያለፉት 10 ዓመታትን ስኬቶቹን በማስቀጠል ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የሆስፒታል ግንባታውን በማጠናቀቅ እንደሚከፍት አስታወቀ፡፡

የማዕከሉን የአስር ዓመታት ስኬትና የቀጣይ አስር ዓመታት ስትራቴጂክ እቅድን በማስመልከት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዋሽንግተን ሄልዝ ኬር ባለአክሲዮንና ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ማርቆስ ፈለቀ እንደገለፁት ዋሽንግተን ሄልዝ ኬር አሉ የተባሉ ስፔሻሊስት ሃኪሞችንና ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎችን በማቀናጀት ጥራት ያለውና አስተማማኝ የህክምና አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነ ጠቅሰው  ባለፉት አስር ዓመታት ከመጀመሪያ ደረጃ የህክምና አግልግሎት ጀምሮ ከፍተኛ እስከሚባል የቀዶ ጥገና ህክምናዎችን በመስጠት ሰፊ ግልጋሎት ለህብረተሰቡ ሰጥቷል ብለዋል፡፡

በተለይም በኮቪድ 19 ወቅት ዋሽንግተን ሄልዝ ኬር ከዋናው የህክምና ማዕከል በተጨማሪ በተለያዩ የከተማችን ሆቴሎች ውስጥ ጊዜያዊ የምርምራ ጣቢያ በመክፈት በርካታ ዜጎች አገልግሎት የሰጠ ሲሆን  በሚሊኒየም አዳራሽ በተቋቋመው የምርመራ ጣቢያ ግለሰቦች ከመኪናቸው ሳይወርዱ ምርምራ እንዲያገኙ መደረጉን  ዶ/ር ማርቆስ አስታውሰዋል፡፡ በተለይም ወደ ውጪ ሀገር ለሚጓዙ መንገደኞች የተቀላጠፈ የኮቪድ ምርምራ ከሚሰጡ የጤና ተቋማት መሀከል ግንባር ቀደሙ ዋሽንግተን ሄልዝ ኬር እንደነበር የጠቀሱት ዶ/ር ማርቆስ በዚህም ከግማሽ ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ መንገደኞች ምርመራ በማድረግ አስተማማኝና በማናቸውም ሀገራት ተቀባይነት ያለው የጤና ምርመራ ሰርተፍኬት መስጠቱን ተናግረዋል፡፡

ዋሽንግተን ሄልዝ ኬር የተመሰረተበትን 10ኛ ዓመት አከበረ

በቀጣይ አስር ዓመታት ዋሽንግተን ሄልዝ ኬር  አገልግሎቱን በማሳደግ ሳህሊተ ምህረት አካባቢ ይገኝ የነበረውን በሻሌ ሆቴል በመግዛት ወደ ሆስፒታልነት የመቀየር ስራው በመጪው አዲስ ዓመት አጠናቆ በአዳዲስ የህክምና መሳሪያዎችና የሰው ሀይል ተደራጅቶ አገልግሎት እንደሚሰጥ የጠቀሱት ዋና ስራ አስፈፃሚው ለህብረተሰቡ የተማላ የህክምና አገልግሎት ከመስጠት በተጨማሪ በልዩ ልዩ የማህበረሰብ አቀፍ የድጋፍ አገልግሎቶች ላይ በመሳተፍ ማህበራዊ ሃላፊነቱን መወጣቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናገረዋል፡፡

በምሽቱ ፕሮግራም የዕለቱን የክብር እንግዳ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዴኤታ ወ/ሮ ሰረህላ አብዱላሂ በበኩላቸው ዋሽንግተን ሄልዝ ኬር  ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ  እያከናወነ ላለው  ተግባር መንግስት አድናቆት እንዳለው ገልፀው በቀጣይነት መንግስት የጤና ተደራሽነትን ለማስፋት እየሰራ ባለው የጤና መድን  ሽፋን ላይ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያከናውን ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በዝግጅቱ ላይ   የባህልና ስፖርት ሚኒሰትር ዴኤታና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

ዋሽንግተን ሄልዝ ኬር  የመጪው አስር ዓመት እቅዱን ይፋ ባደረገበት ምሽት የማዕከሉን አዲስ ሎጎ ያስመረቀ ሲሆን ላለፉት አስር ዓመታት ከማዕከሉ ጋር አብረው ለሰሩ ሰራተኞች የእውቅናና የምስጋና ሰርተፍኬት ተበርክቷል፡፡

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe