251 ኮሚዩኒኬሽን ኤንድ ማርኬቲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ ማህበር ከሚያዘጋጃቸው የተለያዩ ይዘት እና ዓላማ ያላቸው ዝግጅቶች አንዱ የሆነውን አመታዊ የሪል እስቴት እና የቤት ኤክስፖ ለሰባተኛ ጊዜ ከታህሳስ 18 እስከ 20 ቀን 2017 በሸራተን አዲስ ኢንተርናሽናል ሆቴል ለጎብኚዎች ክፍት ተደርጓል።
ኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ አዳጊ ኢኮኖሚ እያስመዘገበች ያለችበት ወቅት በመሆኑ በቤት ልማት ዘርፍም እያሳደገች ያለችውን እድገት ተከትሎ የግሉ ዘርፍ የሚኖረውን ሚና ለማጎልበት እንዲረዳ ታስቦ መዘጋጀት የጀመረው ኢቲ ሪል ስቴት እና ሆም ኤክስፖ የሪል ስቴት አልሚዎችን ከቤት ባለቤቶች፣ ከገዥዎች፣ ከሻጮች፣ እና ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር የሚያገናኝ ብቸኛ ኤግዚቢሽን ነው ተብሏል።
በዘንድሮው ኤግዚብሽን ሻጩን እና ገዢውን ከማገናኘት ባለፈ የፖሊሲ አውጪዎች እና ውሳኔ ሰጪዎች ከአልሚዎች ጋር ተቀራርበው በቤት ልማት እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵያ ያሏትን እድሎች ለመምከር እና በግሉ እና በመንግስት ዘርፍ ድልድይ ለመሆን በማለም የኢትዮጵያ ከተማና ልማት ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን እንዲሁም የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ተወካዮች የተወያዩበት በአይነቱ ከፍተኛ የሆነ የፓነል ውይይት ተካሂዷል።
የ251 ኮሚዩኒኬሽን ኤንድ ማርኬቲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መስራች አቶ አዲስ አለማየሁ እንደገለጹት ‹በዘንድሮው 7ኛው ኢቲ ሪልስቴት እና ሆም ኤክስፖና የውይይት መድረክ ትልቅ ፋይዳ ያለው ክስተት የተዘጋጀ ሲሆን በኢንዱስትሪው ከፍተኛ ተደማጭነት ያላቸው የዘርፉን ተዋንያን አሰባስቧል፡፡ ዘላቂ ል፣ማትን ፈጠራንና ኢንቨስትመንትን የያበረታታ መድርክ ነው› ብለዋል፡፡
በዕለቱ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ ከተማና ልማት ሚንስቴር፣ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ እንዲሁም ጎብኚዎች የተሳተፉበት የፓነል ውይይትና የጥያቄና መልስ መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡

