የማቲዎስ ወንዱ የሕፃናት ካንሰር ፋውንዴሽን መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንዱ በቀለ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ72 ዓመታቸው ትላንት መስከረም 24 ቀን 2019 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ሥርዓተ ቀብራቸውር ዛሬ መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም በቦሌ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ከቀኑ 6 ሰዓት ተፈጸማል።
አቶ ወንዱ በካንሰር ሕመም ያጧቸውን የልጃቸውን የማቲዎስን ስም በመሰየም እ.ኤ.አ. በ2004 ፋውንዴሽኑን ከመሠረቱበት ጊዜ ጀምሮ፣ ይከፈላቸው የነበረውን የመንግሥት የኃላፊነት ቦታ በፈቃደኝነት በመልቀቅ ሙሉ ሕይወታቸውን ለበጎ አድራጎት ሥራ አውለዋል።
ተቋሙ ላለፉት 22 ዓመታት ከ5,000 በላይ ለሚሆኑ የካንሰር ሕሙማንና ቤተሰቦቻቸው የሕክምና፣ የትራንስፖርት፣ የምግብና የሥነ-ልቦና ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።
በተጨማሪም በአገር አቀፍ ደረጃ የካንሰር እና የትምባሆ ቁጥጥር ፖሊሲዎች እንዲወጡ ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከዓለም ጤና ድርጅትና ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ዘጠኝ ታላላቅ ሽልማቶችን አግኝተዋል።
ማቲዎስ ወንዱ ፋውንዴሽን በሕፃናት ጤና፣ በትምባሆና የሳንባ ካንሰር ቁጥጥር ዙሪያ 10 ፕሮጀክቶችን ዘርግቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።
ተቋሙ ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በኦሮሚያ ክልል ሙከ ጡሪ እና በአማራ ክልል አዲስ ዘመን በሚገኙ ሆስፒታሎች የጀመረው ሥራ ውጤታማ በመሆኑ፣ የጤና ሚኒስቴር አገልግሎቱን ወደ 150 ሆስፒታሎች ለማስፋፋት አቅዷል። የሳንባ ካንሰር ፕሮጀክቱም በ36 ሆስፒታሎች ውስጥ የካንሰር ሕክምና እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል።
ፋውንዴሽኑ ትኩረቱን በካንሰር ታማሚዎች ላይ ቢያደርግም፣ ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞችን በመከላከል ረገድ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።
አቶ ወንዱ በቀለ በቅርቡ በኮላንጂዮካርሲኖማ (የሐሞት ቧንቧ ካንሰር) ሕመም ታመው በሕክምና ላይ እንደነበሩ ይታወቃል።
የማቲዎስ ወንዱ ካንሰር ፋውንዴሽን መሥራች አቶ ወንዱ በቀለ ቀብር ሥርዓት ዛሬ ተፈጸመ

