ሰብአውያን ተዋሪዎች (humanistic theorists) የሰው ልጅ ባዶ ሆኖ ሳይሆን ከእምቅ ችሎታ ጋር ወደ እዚህ ምድር መጥቷል ብለው ያምናሉ። አብርሃም ማስሎ (Abraham Maslow) የሚባል አሜሪካዊ ተዋሪ እጅግ ስኬታማ የነበሩ ግለሰቦችን (ለምሳሌ፦ አብርሃም ሊንከን፣ ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ መሀተማ ጋንዲ..ወዘተ) ሕይወት ከተለያዩ ፅሁፎች በማሰባሰብ አጠና። የጥናቱ ሳይንሳዊነት አጠያያቂ ቢሆንም፣ በጥናቱ መሠረት እጅግ ስኬታማ የሆኑ እነዚህ ታላላቅ ሰዎች አያሌ የጋራ ባህርያት ነበራቸው።
ከእነዚህ ውስጥ “ጤናማ” የሚላቸውን 8 ባህርያት እንመልከት፦ አወንታዊነት (optimism) ስኬታማ ሰዎች ህይወትን አጨልመው ሳይሆን በበጎ አይን ይመለከታሉ። እነዚህ ሰዎች እንቅፋት ሲገጥማቸው እንኳ እንደ ማደጊያ መንገድ ይወስዱታል እንጂ በትንሽ በትልቁ አያላዝኑም። ጨዋታ አዋቂነት (sense of humor) እነዚህ ሰዎች በህይወታቸው ችክ ያሉ ደረቆች ሳይሆኑ ጨዋታ የሚያውቁና ፈገግታ ከፊታቸው የማይጠፋ ናቸው። ክፍትነት (open to new experience) ጤናማ ሰው አዲስ አስተሳሰብ ሲሰማ ደስ ይለዋል እንጂ ቱግ አይልም። ክፍትነት ለአዲስ ሰው፣ አሰራር፣ እምነት፣ አስተሳሰብ፣ እና ቴክኖሎጂ ጉጉ መሆንን ያጠቃልላል። ራስን ማወቅ (self-awareness) ጤናማና ስኬታማ ሰዎች ድካማቸውን፣ ብርታታቸውን፣ እንዲሁም የሚጠሉትን ወይም የሚወዱትን ጠንቅቀው የሚያውቁ ግለሰቦች ናቸው።
ራስን መቀበል (self-acceptance) በምድር ላይ ማንም ያለ ጉድለት የተፈጠረ የለም። ጠንካራ ሰዎች ድካማቸውን አውቀው ራሳቸውን ተቀብለው ይኖራሉ ነገር ግን ደካሞች ጉድለታቸውን እያዩ ዘወትር እዬዬ ባዮችና አጉረምራሚዎች ናቸው። አዎንታዊ ግንኙነት (positive relationship) አዳጊ ሰዎች ከብዙ የይምሰል ጓደኝነት ይልቅ ጥቂት የልብ ጓደኞች አሏቸው። ከሚስቱ እና ከጓደኞቹ ጋር ጥሩ ጓደኝነት የሌለው ለውድቀት የቀረበ ዕድለቢስ ነው። ፍቅርና እክብካቤ (loving and caring) በአለማችን ላይ የተነሱ ታላላቅ ሰዎች የፍቅር ሰዎች ነበሩ፤ ግባቸው የሌሎች ስኬት ነበር፤ በህይወት ዘመናቸው ለሰው ኖረው ነበር ለሰው የሞቱት።
በተቃራኒው፣ በህይወት መሰላል ላይ ከታች የቀሩ ሰዎች ለራስ ኖረው ለራሳቸው የሞቱ ስግብግብ ግለሰቦች ናቸው፤ ሰው አይወዱም፤ አይራሩም እንዲሁም ለሰው ግድ የላቸውም ወይም አልነበራቸውም። በሰዎች አስተያየት አይሰበሩም (not paralyzed by other’s opinion) ስኬታማ ሰዎች የራሳቸውን እንዲሁም የሌሎችን ችሎታ እንዲሁም ደካማ ጎን ጠንቅቀው ያውቃሉ፤ ከሌሎች የሚመጡ ትችቶችን ሰምተው የሚሰበሩ ሸምበቆዎች ግን አይደሉም። በህይወት መንገዳቸው የተለያዩ ሰዎች በትችት ከመንገዳቸው ሊያደናቅፏቸው ይሞክራሉ ነገር ግን እንደ ብረት ፅኑ ስለሆኑ ከጉዞአቸው ለአፍታም ቆም የሚሉ አይደሉም።
መደምደሚያ ጤናማ እና የሚያድግ ሰው የሚጫወት፣ ሰው የሚወድ፣ ቀና አሳቢ፣ ለራሱ ጥሩ ግምት ያለው ነው። ቸር ሁኑልን።
ምንጭ፦ ሳይኮሎጂ101

