የቁም ነገር መጽሔት 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓል በድምቀት ተከበረ

ቁም ነገር መፅሔት ለጨረታ ቀርቦም በ400 ሺ ብር በካዲስኮ ሆስፒታል ባለቤት አቶ ሳላዲን ከሊፋ ተገዝታለች፡፡

ከመስከረም ወር 1994 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት 25 ዓመታት ስትታተም የቆየችው ቁም ነገር መፅሔት የተመሰረተችበትን 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል በካፒታል ሆቴል አከበረች፡፡

በዚህ የብር ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል ላይ በርካታ የኪነ ጥበብ ቤተሰቦች የተገኙ ሲሆን በመፅሔቷ ላይ የተስተናገዱ እንግዶች፤ የፅሑፍ አቅራቢዎች፤ ደራሲያን የማስታወቂያ ባለሙያዎችና አስነጋሪዎች የቀድሞውና የአሁኑ የመፅሔቷ ባልደረቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

ልዩ እትም

በተወዳጁ ኮሜዲያን ደረጄ ኃይሌ የመድረክ አጋፋሪነት በተመራው መድረክ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ የመጽሔቱ አሳታሚና ዋና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ ታምራት ኃይሉ እንደተናገረው ምንም ነገር አንድ ተብሎ ሲጀምር መድረሻው ብዙ ውጣ ውረድ ሊኖረው እንደሚችል የታወቀ እንደሆነ ጠቁሞ የቁም ነገር መፅሔት ያለፉት 25 ዓመታት ጉዞም ብዙ ተግዳሮቶችን ያለፈ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ያም ሆኖ ችግሮቹን አልፎ ከመፅሄቷ ቤተሰቦች ጋር በጋራ ተገናኝቶ ክብረ በዓሉን ለማክበር በመቻላችን ፈጣሪያችንን እናመሰግናለን ብሏል፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት ከ2240 በላይ በኪነጥበብና በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ እንግዶች በመጽሔቷ ላይ እንግዶች ሆነው ሃሳባቸውን ማካፈላቸውን ያስታወሰው ጋዜጠኛ ታምራት በዚህ ረጅም ጉዞ ውስጥ ከመፅሔቷ ጎን ለቆሙ አጋሮች በአጠቃላይ ምስጋና አቅርቧል፡፡

የህይወት ዕጣ ፈንታ ሆኖ ከዝግጅት ክፍሉ ባልደረቦች መሀከል 3 ጋዜጠኞች ባለፉት 25 ዓመታት በሞት መለየታቸውን ያስታወሰው ዋና አዘጋጁ 8 ያህል ፅሑፍ አቅራቢ ደራሲያን፤ ጋዜጠኞች እንዲሁም ቁጥራቸው በርካታ አንጋፋና ወጣት የኪነ ጥበብ ሰዎችን በሞት መለየታቸውን በሃዘን አስታውሷል፡፡

የ25ኛ ዓመት የመፅሔቷን ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ በመጀመሪያው እትም ላይ የወጡ 5 እንግዶችን ከ25 ዓመታት በኋላ 25 ጥያቄዎችን በመጠየቅ ልዩ ዕትም መፅሄት መዘጋጀቱንና በዕለቱ ለአንባቢያን መቅረቡን ተናግሯል፡፡

በጋዜጠኛ ታምራት ኃይሉ ልጅ ዳግማዊ ታምራት የስነ ግጥም ንባብና በዳዊት ባንድ የደመቀ የሙዚቃ ዝግጅትና በተጋባዥ እንግዶች አስተያየት የተጀመረው ክብረ በዓል ላይ መጋቢ አዲስ እሸቱ አለማየሁ፤ ጋዜጠኛና የማስታወቂያ ባለሙያ ሳምሶን ማሞ፤ አርቲስት ታምሩ ብርሃኑና አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ ስለ መፅሔቷና ስለ መስራቹ ጋዜጠኛ ታምራት ኃይሉ አበረታች አስታያየቶችን ሰጥተዋል፡፡

ልዩ እትም

በመፅሔቷ የ25 ዓመት ጉዞ  በማስመልከት የመልካም ምኞት መግለጫ ያስተላለፉ ታዋቂ ሰዎችን የተመለከተው ዶክመንተሪ ፊልም ላይ መፅሔቷን የህትመት ወጪዋን ተቋቁማ ለማስቀጠል የሁሉም አካላት ትብብር አስፈላጊ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡ የተዘጋጀውን የዶክመንተሪ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የዝግጅት ክፍሉ ባልደረቦች፤ ፅሁፍ አቅራቢያን የማስታወቂያ ደንበኞችና ጋዜጠኞች የምስጋና የምስክር ወረቀትና የዋንጫ ሽልማት የተበረከተ ሲሆን ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ ፤ ዶ/ር ዘላለም ጌታቸው፤ አቶ ደረጄ ምክሩ፤ ወ/ሮ ራሔል ዘውዱና ዋና ስፖንሰር የሆነው ካፒታል ሆቴል የዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

በመስከረም ወር 1994 ዓ.ም የወጣችው የመጀመሪዋ እትም ቁም ነገር መፅሔት ለጨረታ ቀርቦም በ400 ሺ ብር በካዲስኮ ሆስፒታል ባለቤት አቶ ሳላዲን ከሊፋ ተገዝታለች፡፡ አቶ ሳላዲን ጨረታውን ካሸነፉና መፅሔቷን ከጋዜጠኛ ታምራት ኃይሉ ከተረከቡ በኋላ ባደረጉት ንግግር ቁም ነገር መፅሔት ለሀገራችው በርካታ ቁም ነገሮችን ያበረከቱ ባለሙያዎችን በማውጣት ታሪካቸው ትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆን ስትሰራ መቆየቷን በማስታወስ የመጀመሪያዋን ታሪካዊ የህትመት ውጤት በጨረታ በማሸነፋቸው መደሰታቸውን ገልፀው መፅሄቷን በሆስፒታሉ ውስጥ ሁነኛ ስፍራ በመስቀል ታሪክን እንደሚዘክሩ ተናግረዋል፡፡

Comedian Derege Haile

በመጨረሻም  የተለያዩ አርቲስቶችና ግለሰቦች ስጦታ ያቀረቡ ሲሆን ካስማ ፈርኒቸር ሙሉ የቤት ዕቃ በስጦታ ካበረከተ በኋላ ካፒታል ሆቴል ስፖንሰር ያደረገው የራት ምሽትና የሙዚቃ ዝግጅት ቀርቧል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe