በቅርቡ ደራሲ ይታገሱ ጌትነት ገበየሁ “መንግስቱ ኃይለማርያም – የስደተኛው መሪ ትረካዎች” የተባለ መጽሐፍ አሳትሟል። ደራሲው ዚምባብዌ ድረስ ተጉዞ የቀድሞውን የኢትየጵያ መሪ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያምን በልዩ ልዩ ጉዳዮች ዙሪያ ቃለመጠይቅ አድርጎ ነው መጽሐፉን ያሳተመው።
ፕሬዝንቱ በአንደኛ መደብ ተራኪነት በሚገልጹበት በዚህ መጽሐሩ ውስጥ ታዲያ ስለ ደራሲ በአሉ ግርማ አሟሟት እንቆቅልሽ ዙሪያ አስተያዬት ሰጥተዋል። በመጽሐፉ ከገፅ 301 እስከ 302 “እንቆቅልሹ በአሉ” በሚል ርዕስ ስር የተናገሩት እንዲህ ይነበባል-
“እንቆቅልሹ በአሉ”
በአሉ ግርማ መንግስታችን ውስጥ ካሉት ሙያተኞች አንዱ ነው። ከርሱ ጋር ያለን ግንኙነት እንደ ሌሎቹ የሥራ ባልደረቦቼ ሁሉ ያለ ነው። እርግጥ ነው አሁን ጊዜው ረዝሟል፤ በተለይ አሁን ካለሁበት ሁኔታ አንጻር ሁሉንም ነገሮች በጥልቀት ለማስታወስ ይቸግረኝ ይሆናል። በአሉ ግርማ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ነበር የሚሰራው።
ያን መጽሐፉን (ኦሮማይ) ከጻፈ በኋላ በርካታ ጫጫታዎች ተነስተው፣ ሥራው ላይ መቆየት የማይችልበት ሁኔታ ተፈጠረ፤ ጥቂት ቆይቶ ድንገት “ጠፋ” ተባለ። በዚህ ዙሪያ እንዴት ሊሆን ይችላል? የሚለውን ሳስብ የኔ ግምት በወቅቱ “መኮንኖቹም ሆነ ሌላ ሌላዎቹን የሚያስቀይም ነገሮች ተናግሯል” በሚል ጠልተውት፣ ተቆጥተውበት ነበር። በወቅቱ በኔ በኩል እጅግ የስራ ጫና ነበረብኝ፤ እሱ ያላቸውንና የሚላቸውን እያንዳንዷን ነጥብ ተከታትዬ ለማየትም ሆነ ለመስማት ሁኔታዎች አይፈቅዱልኝም ነበር።
ስገምት ግን በበአሉ መጥፋት ዙሪያ አንድ ‘ኮንስፓይረሲ’ ያለ ይመስለኛል። ተሰወረ የሚለው መረጃ ቢደርሰኝም፣ በርከት ያልነው የመንግስቱ አካላት በዚህ ጉዳይ ላይ ምን እንደ ተፈጠረ ጥርት ያለ መረጃ አለን ብዬ አላምንም። ሆኖም “ስማችንን አጠልሽቷል፣ ክብራችንን አዋርዷል” ብለው ያመኑ መኮንኖች ከደህንነቱ አካላት ጋር ተባብረው ያስወገዱት ይመስለኛል። በአሉ ምንድነው የሆነው? የት ነው መጨረሻው? የሚለው እንዲሁ ዱካ የሌለው ታሪክ ነው የሆነው።
በአሉ ግርማ የጻፈው መጽሐፍም ሆነ ያደረጋቸው ነገሮች ፈጽሞ ለሞት ያደርሰዋል የሚል እምነት የለኝም። ሆኖም በግለሰብ ደረጃ አንዳንድ ሰዎች ቂም የያዙበት ሰዎች የሰሩት ሴራ የበአሉን መጨረሻ እንዲህ ያደረገው ነው የሚመስለኝ። አስረግጬ የምናገረው የበአሉ መጥፋት ጉዳይ ለኛም የተሰወረ ነው። በወቅቱ የበአሉን ባለቤት ሁሉ አነጋግሬያለሁ። ለሁላችንም እስከዛሬ እነቆቅልሽ ሆኖ የቀረ ታሪክ ነው በአሉ።
ወቅቱ እንግዲህ አብዮት ነው፤ ጦርነትም ሆነ ትኩረት የሚወስዱ በርካታ ጉዳዮች ነበሩ። በግራም ሆነ በቀኝ አንዳንድ ሰዎች አደጋ ወይም ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል። ያንን ሁኔታና ወቅት ተጠቅመው ነው በአሉን ያስወገዱት የሚል ነው ጥርጣሬዬ።
እርግጥ ነው ይሄን በተመለከተ በትክክል ማነው ያደረገው ይሄን? ብባል ግን እርግጠኛ ሆኔ የምናገረው በማስረጃ የተደገፈ ነገር የለኝም። ግምት ሊኖረኝ ይችላል፤ ግምትን ግን ይዞ የግለሰቦችን ስም ማንሳት አግባብ አይደለም።
(መንግስቱ ኃይለማርያም – የስደተኛው መሪ ትረካዎች፣ በደራሲ ይታገሱ ጌትንት ገበየሁ፣ ገጽ 301-302)
የበአሉ መጥፋት ጉዳይ ለኛም የተሰወረ ነው – ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም

