በመካከለኛው ምስራቅ በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተከትሎ፣ የቡድን 7 አገራት የፋይናንስ ሚኒስትሮች የነዳጅ ክምችታቸውን ወደ ገበያ ስለሚለቁበት ሁኔታ ዛሬ አስቸኳይ ስብሰባ እንደሚያደርጉ ተሰማ።
እንደ ፋይናንሻል ታይምስ ዘገባ፣ የዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ ኃላፊ በሚገኙበት በዚህ ስብሰባ ላይ ከ300 እስከ 400 ሚሊዮን በርሜል የሚደርስ ነዳጅ ከክምችት እንዲወጣ ሊወሰን ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ መረጃ ይፋ መደረጉን ተከትሎ በዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ ላይ መጠነኛ የዋጋ ቅናሽ የታየ ቢሆንም፣ የብሬንት እና የደብሊው ቲ አይ የነዳጅ ዋጋ አሁንም ከአንድ በርሜል 100 ዶላር በላይ ሆኖ እየተሸጠ ይገኛል።
አገራቱ ሊለቁት ያሰቡት የነዳጅ መጠን እ.ኤ.አ. በ2022 ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ በፈጸመችበት ወቅት ገበያውን ለማረጋጋት ከወጣው 240 ሚሊዮን በርሜል እጅግ የላቀ ነው።
የዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ ኃላፊ ፋቲህ ቢሮል ከጥቂት ቀናት በፊት “በገበያው ላይ በቂ ነዳጅ ስላለ ተጨማሪ ክምችት መልቀቅ አያስፈልግም” ብለው የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን ሁኔታዎች ተቀይረው የአሜሪካን ጨምሮ ሦስት የኤጀንሲው አባል አገራት የጋራ የነዳጅ ክምችት እንዲለቀቅ ፍላጎት አሳይተዋል።
አሜሪካ በሩሲያ ድፍድፍ ነዳጅ ላይ ጥላው የነበረውን አንዳንድ ማዕቀቦች በማንሳት ነዳጁ ወደ ህንድ እንዲላክ ብትፈቅድም፣ ይህም ቢሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የነዳጅ አቅርቦት እጥረት ሊቀርፈው እንዳልቻለ ተጠቁሟል።
የኢራን እና እስራኤል ጦርነት በሆርሙዝ የባህር ሰርጥ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት መፍጠሩን ተከትሎ፣ የሳውዲ አረቢያ የነዳጅ ምርት በገበያው ላይ በፈለገው መጠን እንዳይቀርብ አድርጎታል።
(Capital)

