የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ማንም ሀማስን የሽብር ቡድን ነው ብሎ ለእኛ መናገር አይጠበቅበትም፤እኛ ከቡድኑ መሪዎች መነጋገራችንን አንተውም አሉ። ቱርክ በይፋ ከሃማስ መሪዎች ጋር መነጋገሯን ትቀጥላለች ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ እሀድ እለት በአንካራ ባደረጉት ንግግር ማንም ሃማስ የሽብር ድርጅት መሆኑን እንዲነግረን አንሻም ቱርክ በይፋ ከቡዱኑ ሰዎች ጋር የምትነጋገርና የምትደግፍ አገር ናት ብለዋል።
ሀማስ በአሜሪካ:በእስራኤል:በዩናይድኪንግደም:በአውሮፓ ህብረት:በካናዳ:በጃፓን:በአውስትራሊያ:በኒውዝላንድና በሌሎች በርካታ አገራት የሽብር ቡድን ተብሎ የተፈረጀ ነው።
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ግን ሀማስ የሽብር ቡድን ሳይሆን መሬታቸው በሌሎች እንዳይወሰድ ቅዱስ ጦርነት እያደረገ የሚገኝ ሀይል ነው ብለዋል።
አክለውም ኔትንያሁና መንግስታቸው በጋዛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየፈፀሙ ነው ብለው ስማቸውም ከሂትለር:ከሞሶሎኒ እና ከእስታሊን ቀጥሎ የሚጻፍ መሆኑን መናገራቸውም ታይምስ ኦፍ እስራኤል አስነብቧል።
ፕሬዝዳንት ጣይብ ኤርዶጋን የጋዛው ጦርነት ከተሳበት ጊዜ አንስቶ በእስራኤል ላይ የበረታ ተቃውሞ እያሰሙ ነው የሚገኙት።
ካለፉት አምስት ወራት ጀምሮ ደግሞ እስራኤልን እንደ ሽብርተኛ መንግስት አድርገው የሚቆጥሯት ሲሆን በጋዛም የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመች ነው በማለት ይከሷታል።
እንዲያውም ከወራቶች በፊት ፕሬዝዳንቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከሂትለር ጋር በአንድ ሚዛን በማስቀመጥ ፍረጃቸውን ሰጥተውም ነበር።
በዚያን ወቅትም ፕሬዝዳንቱ መንግስታቸው ከሃማስ ጋር ያለውን ጠንካራ ግንኙነት እንደሚያስቀጥልና ለቡድኑ ሰዎችም መጠጊያ መሆኗን እንደምትገፋበት መናገራቸውም ይታወሳል።
ከዚህ ቀደም ቱርክ በምድሯ የሃማስ የፖለቲካው ክንፍ ሰዎች ብቻ እንደሚገኙ የገለፀች ቢሆንም፤እስራኤል ግን የቡድኑ የወታደራዊ ክንፉ ሰዎችም ስለመኖራቸው መረጃው እንዳለው ገልጾ ነበር።
ከዓመታት በፊት ኤርዶሃን የአይሁድ መንግስት የሂትለር መንፈስ በጋዛ እንዲቀጥል እያደረገ ነው የሚል ንግግር ተናግረው እንደነበረም የታይምስ ኦፍ እስራኤል ዘገባ ያስረዳል።
በ2018 ሁለቱም አገራት አምባሳደሮቻቸውን መጥራታቸው እንዲሁ አይዘነጋም።
በኦገስት 2022 ደግሞ ሻክሮ የነበረውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ማደሳቸውን ይፋ ያደረጉበት ወቅት ነበር።
የጋዛው ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ወዲህ ግን ሀገራቱ ዳግም ወደ ውጥረት ገብተዋል። ቱርክ ከእስራኤል ጋር የነበራትን የንግድ ግንኙነት በሙሉ እንዲቋረጥ አድርጋለች።/
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን በይፋ ከሃማስ መሪዎች ጋር መነጋገሯን ትቀጥላለች አሉ

