የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ለመጀመሪያው የውጭ የኢንቨስትመንት ባንክ ፈቃድ ሰጠ
የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ለናይጄሪያው ዩናይትድ ካፒታል ፋይናንሻል ሰርቪስ ኃ.የተ.የግ.ማህበር የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪነት ፈቃድ መስጠቱን አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን የፈቃድና ምዝገባ ኃላፊ አቶ እንድሪስ ሰልማን ለጋዜጣ ፕላስ እንደገለጹት፣ የናይጄሪያው ዩናይትድ ካፒታል ግሩፕ አባል ኩባንያ ለሆነው ዩናይትድ ካፒታል ፋይናንሻል ሰርቪስ ኃ.የተ.የግ.ማህበር የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪነት ፈቃድ ሰጥቷል ብለዋል።
ተቋሙ በኢትዮጵያ ውስጥ ተቀጥላ ኩባንያ በማቋቋም እንዲንቀሳቀስ ፈቃድ የተሰጠው የመጀመሪያው የውጭ ኢንቨስትመንት ባንክ መሆኑንም ገልጸዋል።
ተቋሙ በርካታ ሂደቶችን ካለፈ በኋላ ፍቃድ የተሰጠው መሆኑን ጠቅሰው፣ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እንደማንኛውም ባለሀብት የሚጠበቅበትን መስፈርቶች አሟልቶ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ባንኮች የሚሰሯቸው ሥራዎች ተመሳሳይ መሆናቸውን በመግለጽ፣ የማማከር አገልግሎት፣ የግብይት አማካሪ፣ ውህደትን የተመለከቱ አገልግሎትን ጨምሮ በሰነድ ሙዓለ ነዋይ ተመዝግበው ለደንበኞቻቸው የግብይት አገልግሎት መስጠት እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
የተሰጠው ፈቃድ ድርጅቱ በኢንቨስትመንት ባንክ ዘርፍ ስር እንዲሠራ የሚፈቅድ መሆኑን ጠቅሰው፣ የካፒታል ገበያ ተግባራዊነትና ልማት ቀጣይነት ያለው ዕድገት የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
እንደ ዩናይትድ ካፒታል ያለ የፓን-አፍሪካዊ ተቋም ወደ ገበያው መግባቱ በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ዕድገት ላይ ታሪካዊ ምዕራፍ እንደሆነ ገልጸው፤እየተከናወኑ ባሉ የማሻሻያ እርምጃዎች እያደገ ላለው የሀገሪቱ የፋይናንስ ሥነ-ምህዳር ጠንካራ እምነት መኖሩን እንደሚያሳይ አመልክተዋል።
በሀገሪቱ ውስጥ የተፈቀደላቸው 18 የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፣እነዚህም ሰባት የኢንቨስትመንት ባንኮች፣9 የሰነደ ሙዓለ ነዋይ ኢንቨስትመንት አማካሪዎች፣2 የሰነደ ሙዓለ ነዋይ ገበያ አከናዋኝ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

