የአልቃይዳው መሪ የኦሳማ ቢን ላደን የፕሮፖጋንዳ ክፍል ሀላፊ የነበረው እና በጎርጎሪያኑ መስከረም 11፣ 2001 በዩናይትድ ስቴትስ የተፈጸሙትን የሽብር ጥቃቶች ዋና አቀናባሪ ተብሎ የተጠረጠረው ካሊድ ሼክ መሐመድ የፍርድ ቤት ሊቀርብ ቀነ ቀጠሮ ተሰጥቶታል። በአልቃይዳ ከፍተኛ አባልነት እንዲሁም ሌሎች በርካታ ገዳይ የሽብር ጥቃቶችን እንዳቀደ በሰፊው የሚነገርለት ካሊድ ሼክ መሐመድ በጎርጎሪያኑ 2003 ተይዞ ኩባ በሚገኘው የዃንታናሞ ቤይ እስር ቤት ለ20 ዓመታት ያህል በእስር አሳልፏዋል።የአሜሪካ የአየር ኃይል ዳኛ ረቡዕ ዕለት መሐመድ እና ሶስት ተከሳሾች በጎርጎሮሳዊውሰኔ 2028 በወታደራዊ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ አዟል።
ሮይተርስ እንደዘገባው ሂደቱ ለረጅም ጊዜ እንዲዘገይ የተደረገው ከስቅይት በኋላ የሚሰጡ የእምነት ክህደት ቃሎች ላይ በሚነሳው የሕግ ክርክር፣ ፍርድ ሊሰጥ የሚችልበት ቦታ የማግኘት ጉዳይ፣እንዲሁም የመስከረም 11 የሽብር ጥቃቶች ዋና አቀነባባሪ ተብሎ በሰፊው በሚታሰበው ሰው ላይ የነበረው ኃይለኛ ቁጣ የተነሳ ነው።መሐመድ ቀደም ሲል የሞት ቅጣትን ለማስቀረት ጥፋተኛ መሆኑን አምኖ ለመቀበል የተስማማበት የክስ ስምምነት ባለፈው ዓመት ውድቅ ተደርጓል።አዲሱ ችሎት መሐመድ፣ ዋሊድ መሐመድ ሳሊህ፣ ሙባረክ ቢን አታሽ፣ ሙስጠፋ አህመድ፣ አደም አል ሀውሳውዊ እና አሊ አብዱል አዚዝ አሊ በአሜሪካ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ችሎት የሚቀርቡ ሲሆን፤ በችሎቱ ደግሞ የጦር አባላት በዳኝነት ይሰየማሉ።
በጎርጎሪያኑ 1965 በኩዌት የተወለደው ሼክ መሐመድ ፤በ1986 ከአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ዲግሪ ከማግኘቱ በፊት የፀረ-ሶቪየት ፅንፈኛ ቡድኖችን ይደግፍ እንደነበር ይነገራል።ለኳታር መንግስት ለተወሰነ ጊዜ በመሐንዲስነት ሰርቷል። እንደ የአሜሪካ የስለላ ወኪሎች ገለጻ፣ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ በአሜሪካ እና በእስያ መካከል የሚጓዙ አውሮፕላኖችን ለማፈንዳት በተደረገ ሴራ ተሳትፏል፣ነገር ግን ጥቃቱ አልተሳካም ነበር።
ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ከአልቃይዳ መሪ ኦሳማ ቢን ላደን ጋር እንደተገናኙ ይታመናል። የቡድኑ የፕሮፓጋንዳ ኃላፊ እንደመሆኑ መጠን፣ በ1993 የዓለም የንግድ ማዕከል የቦምብ ፍንዳታዎችን፣ በ2002 በኢንዶኔዥያ የባሊ ፍንዳታዎችን፣ የአሜሪካ ጋዜጠኛ ዳንኤል ፐርልን ግድያ እንዲሁም የአሜሪካውን የመስከረም 11 የሽብር ጥቃት በማቀድ ረገድ እገዛ አድርጓል ተብሎ ተከሷል።
የአሜሪካውን የመስከረም 11 የሽብር ጥቃት ዋና አቀናባሪ ተብሎ የተጠረጠረው ሰው ከ20 ዓመት በኋላ ፍርድ ቤት ሊቀርብ ነው
SourceDW

