የአጥንት መሳሳትና መፍትሔው

ለዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት/WHO/ ባወጣው መረጃ መሰረት 2001እስከ 2021እ.ኤ.አ /ቦን ኤንድ ዲሄድ/ በሚል ባደረገው ጥናት፤ በአንድ ሀገር ያለውን የአጥንት ችግር ለማወቅ አምስት ነገሮችን አቀምጧል፤ በተለያየ ምክንያት የአጥንት መሰበር ፣ የወገብ ህመም ፣ የቁርጥማት በሽታ፣/ሮማንቲውል አል ትራይዝ/ ወይም እግርና እጅን የሚያደነዝዝ በሽታ እና የአጥንት መሳሳት ናቸው፡፡ እነዚህን አምስት በሽታዎች በማየት ምን ያህል የአጥንት ችግር እንዳለ ማወቅ ይቻላል ሲል ጥናቱ ያሳያል፡፡ በተለይ ችግሩ ባላደጉ ሀገራት ላይ ጎልቶ የሚታይ ሲሆን ለጉዳዩ ግን በቂ ትኩረት ተሰጥቶት እንዳልተሰራም ይገልጻል፡፡
በሃገራችን የችግሩ መጠን ምን ያህል እንደሆነ የሚያሳይ ጥናት ባይኖርም ፤ለችግሩ መፈጠር አንዱ ምክንያት የሆነው በአጥንት ላይ አደጋ መድረስ፤ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ባለው የትራፊክ አደጋ እና ራሱን ችሎ በቂ ህክምና የሚሰጥበት የህክምና ተቋም ካለመኖር አንጻር የችግሩን አሳሳቢነት መገመት አያዳግትም፡፡ እኛም የችግሩን አሳሳቢነት በማየት ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት/WHO/ ካስቀመጣቸው ከአምስቱ የአጥንት ችግሮች መካከል አንዱ በሆነው ‹የአጥንት መሳሳት› ላይ በቅርቡ ተመርቆ ስራ ወደ ጀመረው ‹ዳኑ› የአጥንት ህክምና ሆስፒታል በመሄድ የሆስፒታሉን ባለቤትና ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑትን ዶ/ር ኤልያስ አህመድ አነጋግረናቸዋል፡፡
ቁም ነገር፡- የአጥንት መሳሳት ችግር መንስኤው ምንድነው?
ዶ/ር ኤልያስ፡- የአጥንት መሳሳት ችግር በተለያዩ ምክንያቶች ይከሰታል፤ ዋና ዋና የምንላቸው አራት ምክንያቶቹ ግን አንደኛ በዕድሜ የሚመጣ ሲሆን፤ በተለይ በሴቶች ላይ እድሜያቸው ከ45 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች የወር አበባ መቆምን ተከትሎ ከሆርሞን ጋር በተያያዘ ችግር የአጥንት መሳሳት ያጋጥማችዋል፡፡ ከዚሁ ከዕድሜ ጋር ተያይዞ ከሚመጣ የአጥንት መሳሳት ሳንወጣ ሁለተኛው የሚከሰትበት መንገድ በወንድም ሆነ በሴቶች ወይም በሁለቱም ፆታዎች ላይ ከ65ዓመት በኋላ ችግሩ ይፈጠራል፡፡ በሴቶቹ ላይ ተጨማሪ ሁለተኛ ጉዳት ይሆናል ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ መደሀኒት ከመጠቀም ይመጣል ፡፡ ለምሳሌ እንደ አስም እንዲሁም ሌሎች የተለያዩ በሽታዎች የሚሰጡ መደሀኒቶችን ለረጅም ጊዜ በተከታታይ መጠቀም የአጥንት መሳሳትን ያስከትላል፡፡
ሦስተኛው የተለያዩ የአጥንት መሳሳትን የሚያስከትሉ በሽዎችም አሉ፡፡ አራተኛው አይነት የአጥንት መሳሳት ችግር የሚያስከትለው ያለ መንቀሳቀስ ነው፡፡ አጥንት በባህሪው አንዴ ተሰርቶ የሚቀመጥ ነገር አይደለም ፡፡ ሁልጊዜ ይጨመርበታል፤ እንዲሁም ይቀነስለታል፤ በአሁኑ ከላይ ካለው የአጥንት ክፍል ይነሳለትና ከውስጥ ባለው የአጥንት ክፍል ደግሞ ይጨመርባቸዋል፡፡ በሚቀጥለው ደግሞ ከውስጥ ያለው አሮጌው ክፍል ተነስቶ አዲስ ከላይ ይጨመርበታል፡፡ ሁልጊዜም ተከታታይ የሆነ ሂደት ነው ያለው፡፡ ያ እንዲሆን የሚያደርግው ደግሞ የሰውየው ያንን ነገር የመጠቀም ሁኔታ ነው፡፡ አንድ ሰው እግሩን ሳያንቀሳቅሰው ለሦስት ወር ያህል ቢያቆየው በጣም ብዙ ይቀነስበታል፡፡ ምክንያቱም ሰውነታችን ኃይል ሲያከፋፍል እግራችንን የማንጠቀምበት ከሆነ ለእግራችን የሚያቀርበውን ኃይል ቀንሶ ሌላ አገልግሎት ላይ ለምናውለው አካላችን ያውለዋል፡፡ እግራችንን እየተጠቀምንበት ስላልሆነ እንደ ካልሲየም ፣ፋይቨር እንዲሁም ሌሎችንም ለአጥንት አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን ደረጃ በደረጃ ይቀንስብናል፡፡ ነገር ግን እግሩን እየተጠቀመበት ወይም በቂ እንቅስቃሴ የሚያደርግበት ከሆነ ይበልጥ አስፈላጊ ነገሮችን በማቅረብ ያወፍረዋል፡፡ ሰውነታችንን ልብ ብለን ብንመለከተው ለምሳሌ ታፋችን ይወፍርና ወደታች ወረድ ብሎ ይቀጥናል፤ ቀጥሎ ደግሞ ባታችን ላይ ይወፍራል፤ ይህ የሆነው ያለምክንያት ለቅርጽ ሳይሆን የሰውነታችን አብዛኛው ክብደት የሚያርፍበትና የምንቀሳቀስበት ስለሆነ ነው፡፡
ከመጠቀም ወይም ከመንቀሳቀስ ጋር በተያያዘ አጥንት ብቻ ሳይሆን መገጣጠሚያዎች እና ጡንቻም ሦስት ሳምንትና ከዚያ በላይ በበቂ ሁኔታ ካልተጠቀምንበት 20 % ያህል የሚያስፈልጉ ነገሮች ይነሱብናል፡፡ በዚህም የተነሳ የአጥንት መሳሳት ችግር ይከሰታል፡፡
ቁም ነገር፡- የአጥንት መሳሳት ምልክቶቹ ምንድ ናቸው ? ቸግሩ ያጋጠማቸው ሰዎችስ ምን አይነት ህመም ይሰማቸዋል?
ዶ/ርኤልያስ ፡- የሚሰማቸው ህመም እጅና እግርን ከፍተኛ ቁርጥማት ፣ከፍተኛ ድካም፤በቀላሉ መሰበር እና መደንዘዝ ነው ፡፡ የአጥንት መሳሳት ችግር ያለባቸው ብዙ ጊዜ ስብራት ያጋጥማቸዋል፡፡ በብዛት ስብራቱ የሚከሰትበት ቦታ ደግሞ ፤ የወገብ አከርካሪ (ስፓይናል ኮርድ)፣ የእጅ አንጓ እና የታፋ መጋጠሚያ ላይ ነው፡፡ በወገብ አከርካሪ (ስፓይናል ኮርድ ) ላይ በቀላሉ ታክሲ ውስጥ እንኳን ሲንገጫገጭ የመሰበር አደጋ ያጋጥማል፡፡አንዴ ከተሰበረ በኋላ ደግሞ በህክምናውም ቢሆን ወደ ቀድሞው ቦታው መመለስ አይቻልም፡፡ እጅ ላይ ደግሞ ትንሽ ጫና አብዝተው ሲደገፉ እንኳን የመሰበር ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡
ቁም ነገር፡- ችግሩ ላጋጠማቸው ምንድነው የሚደረግላቸው ህክምና?
ዶ/ርኤልያስ፡- መጀመሪያ / supplement / መስጠት ነው ፡፡ በተለይ በዕድሜ ለሚከሰት የአጥንት መሳሳት አንደኛው ምክንያት ለአጥንት የሚያስፈልጉትን ንጥረ ነገሮችን ካለማግኘትነው፡፡ አንድ ወጣት ይንቀሳቀሳል ፣የተለያዩ አይነት ምግቦችን የመመገብ ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ በዕድሜ የገፉ ሰዎች ግን አንደኛ እንቅስቃሲያቸው የተገደበ ነው ፣ የሚያስፈልጋቸውን ያህል ምግብ ላያገኙ ይችላሉ ፣ቢያገኑ እንኳን የመመገብ ፍላጎታቸው ብዙም ላይሆን ይችላል ፤አንድ ሰው ደግሞ ሳይንሱ እንደሚለው ከሆነ በቀን ውስጥ 1300 ሚሊ ግራም ካልሲየም ያስፈልገዋል፡፡ በዚህ ዕድሜ ባሉ ሰዎች ግን በተሰራ ጥናት የሚያገኙት የካልሲየም መጠን ከሚያስፈልገው 1300ሚሊ ግራም ውስጥ 700 ሚሊ ግራም ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ለዚህ ህክምናው የሚሰጣቸው መፍትሔ /supplement / ኪኒኖች እንዲወስዱ ማድረግ ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ሳይሰበሩ በፊት ከሆነ ነው፡፡ ከተሰበሩ ደግሞ የሚወስዱት / supplement / እጥፍ ነው የሚሆነው፡፡ ሌላው ለቁርጥማትና ለህመም ማስታገሻዎች ይሰጧቸዎል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ ከነገ ዛሬ ይሻለኛል በማለት ዘግይተው ሲመጡና አጥንት በጣም ሲሳሳ የሚሰጥ /ቦን ቪቫ/ የሚባል መዳህኒት አለ፡፡ ጠቀሜታው የሚወሰደው ካልሲየም በቀጥታ ወደ አጥንት ቶሎ ዘልቆ እንዲገባ የሚያደርግ ነው፡፡ ነገር ግን ዋጋው እጅግ በጣም ውድ ነው፡፡ በወር አንድ ፍሬ ኪኒን ሲሆን የሚወሰደው ይህ አንድ ኪኒን ዋጋው አንድ ሺህ አንድ መቶ ብር ነው፡፡
ቁም ነገር፡- እነዚህ የሚሰጧቸው / supplement / ኪኒኖች ፤ተጨማሪ ምግብ / food supplements/ ከሚባለው ጋር አንድ ናቸው?
ዶ/ርኤልያስ፡- አዎ አንድ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ እኛ የምናየው /supplement/ ሆነ ተጨማሪ ምግቦች /food supplements/ በውስጡ የያዘውን የተጣራ ካልሲየም ስንት ይይዛል የሚለውን ነው፡፡ የተጣራ ካልሲየሙ የሚፈለገውን ያህል ከያዘ፤ ተጨማሪ ምግቦቹ /food supplements/ መኖራቸው ጥሩ ነው ይደግፈዋል፡
ቁም ነገር፡- ችግሩ ከመከሰቱ በፊትስ መከላከል ይቻላል?
ዶ/ርኤልያስ፡- በዕድሜም ሆነ በሌላ ምክንያቶች ለሚመጣ የአጥንት መሳሳት ችግር ለመከላከል እነዚህን ሰፕለመንተሪዎች መውሰድ ነው፡፡ ዕድሜ ሲገፋ በተቻለ መጠን ስብራት እንዳይደርስ ጥንቃቄ ማድረግ፡፡ በተለይ ከዕድሜ ጋር ተያይዞ ለሚመጣ ችግር ስብራት ካላጋጠመ በስተቀር ሀኪም ቤት መሄድ አያስፈልግም ፡፡ ባደጉት ሀገራት በራዲዮም ፣በመጽሔት እና በቴሌቭዥን በመሳሰሉት ሚዲያዎች ስለችግሩና ምን ማድረግ እንዳለባቸው ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስለሚሰጠው የሚያስፈልገውን / supplement /ራሱ ከገበያ በመግዛት ይጠቀማል፡፡
ቁም ነገር፡- በአጠቃላይ ህብረተሰቡ ስለ አጥንት ጉዳት ማወቅ አለበት የምትሉት ነገር ምንድነው ?
ዶ/ር ኤልያስ፡- የአጥንትና የመጋጠሚያ ችግሮች ላይ አደጋ በሚፈጠርበት ጊዜ ወዲያው ህክምና ማግኘትና ዘግይቶ ሲታከም ሂደቱና ውጤቱ አንድ አይደለም፡፡ ስለዚህ ሰዎች ወዲያው ችግር እንደተከሰተ ወይም ህመም እደተሰማቸው በባለሙያ መታየት አለባቸው፡፡ ህክምናም ካገኙም በኋላ ጤንነታቸውን መከታተል የሐኪሙ ብቻ ሃላፊነት ብቻ ሳይሆን ታካሚዎቹም እኩል ተሳትፎ ማድረግ አለባቸው ፡፡ አሁን ዘመኑ የቴክኖሎጂ ነው ፡፡ ቶሎ ቶሎ ወደሐኪም መሄድ እንኳን ባይችሉ ስለጉዳዩ ኢንተርኔት ላይ ገብተው ማንበብ ይችላሉ፡፡
አንድ ታካሚ የህክምና ሂደቱ ላይ ተሳትፎ ሲያደርግ ውጤቱ ጥሩ ይሆናል፡፡ መቼ ነው መርገጥ ያለብኝ፣ መቼ ነው ማንቀሳቀስ ያለብኝ፣ እስከ መቼ ነው መደሀኒት መጠቀም ያለብኝ፣ ምንድ ነው መመገብ ያለብኝ የሚለውን መጠየቅ አለበት፡፡ ለምሳሌ የእጅ ወይም የእግር ስብራት ሲያጋጥም መጀመሪያውኑ የምግብ ችግር የሌለበት ሰው ብዙም ከወትሮው የተለየ ምግብ አያስፈልገውም፡፡ ነገር ግን ግዴታ ምግብ መብላት እንዳለበት ታስቦ ቶሎ እንድንጠገን በማለት ሰዎች ብዙ ይወፍራሉ፡፡ ያ ይበልጥ ጫና ነው የሚፈጥረው፤ አለመንቀሳቀሱ አለ፣በዛላይ ምግብ በጣም ይመገቡና ይወፍራሉ የዚህን ጊዜ ሌላ ችግር ነው የሚፈጠረው፡፡ ዋናው ነገር እነዚህን ችግሮች ለማስወገድ ማወቅ የሚያስፈልገው ምንድነው የተከሰተው?፣ምንድነው የተደረገልኝ ? ፣ ከዚህ በኋላስ ምን ማድረግ አለብኝ? የሚለውን ማወቅ ነው፡፡
ቁም ነገር፡- አመሰግናለው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe