የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ምክርቤት በመላዉ ሀገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ ተቋማትን እና በሺዎች የሚቆጠሩ የሚዲያ ባለሙያዎችን በመወከል ስድስት ቁልፍ አጀንዳዎችን ለኮሚሽኑ አስረክቧል።
ዛሬ ማለትም ጥር 29፤ 2017 ዓ.ም. ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የቀረቡት እነዚህ አጀንዳዎች አካዳሚዎችን፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን እና አለም አቀፍ አጋሮችን ያካተተ ሰፊ ምርምር፣ ምክክር እና መረጃ መሰብሰብ ውጤቶች መሆናቸው ተመላክቷል።
ይህን ተከትሎ ምክርቤቱ በኢትዮጵያ የሚዲያ ገጽታ ውስጥ ያሉትን ቁልፍ ተግዳሮቶች እና አድሎች ሁሉን አቀፍ ግምገማ የሚያንፀባርቅ መሆኑን በመግለፅ የሚዲያ ዘርፉን ከብሔራዊ ውይይቱ ግቦች ጋር ለማጣጣም ተግባራዊ ምክሮችን ማቅረብን አስታውቋል።
በሂደቱ የፓናል ውይይቶች፣ ገለጻዎች እና የአካዳሚክ ስነፅሁፍ፣ የፖሊሲ ሰነዶች እና አለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን የገመገመ ሲሆን በመጨረሻም 79 ቁልፍ ጉዳዮችን በመለየት ወደ 19 ቅድሚያ የሚሰጣቸው ርዕሰ ጉዳዮችን በመለየት በመጨረሻም ስድስት ዋና ዋና አጀንዳዎች በመለየት አጠናቅቋል።
ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንዲቀርቡ ከተለዩት አጀንዳዎች መካከል የህዝብ ሚዲያ አስተዳደርን በሚመለከት ፣ የፋይናንስ ዘላቂነትና የማስታወቂያ ኢፍትሃዊነት ፣ የመረጃ ነፃነት ፣ መረጃ የማግኘት መብት እንዲሁም ስርጭት እና ተደራሽነትን የተመለከቱ ዝርዝር ጉዳዮች ይገኙበታል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክርቤት ስድስት ቁልፍ አጀንዳዎችን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረከበ

