የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሰባት ቢሊየን 735 ሚሊየን ብር አጭበርብረውኛል ባላቸው በ14 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ፤ ክስ ከተመሰረተባቸው ግለሰቦች መካከል ሁለቱ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ሰራተኞች መሆናቸውን አስታውቋል። አድራሻቸው አዲስ አበባ መሆኑ የተገለጹ የደህንነት ተቋሙ ሰራተኞች ንጉሴ እምሩ ጉሪኖ እና መሀመድ ነጋሽ ገሰሰ (ቅፅል ስም ዋለልኝ) የተባሉ መሆናቸውም በክሱ ላይ ተጠቅሷል።
አዲስ ስታንዳርድ የተመለከተው በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ፀረ ሙስና ወንጀል ችሎት የቀረበው የክስ ዝርዝር እንደሚያሳየው ባንኩ ለመሰረተው ክስ 20 የሰው እና 24 የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል። ከ14ቱ ተከሳሾች ውስ) 13 በእስር ላይ ይገኛሉ ተብሏል።
የክሱ መዝገብ እንደሚያስረዳው ተካሳሾቹ “በዋና ወንጀል አድራጊነት እና ስልጣንን አለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል” ነው የተመሰረተባቸው።
በተያዘው አመት 2017 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ መገናኛ ብዙሃን “በኢትዮጵያ ንግድ ባንከ የውስጥ አካውንት ውስጥ ተቀምጦ የነበረ ከ7 ቢሊየን ብር በላይ መዘረፉ ተገለፀ” በሚል ሰፊ ሽፋን የተሰጠው ዘገባ ማቅረባቸው ይታወሳል፤ ይህንንም ተከትሎ ባንኩ ምንም ገንዘብ አልተዘረፍኩም ሲል መግለጫ በማውጣት አስተባብሎ ነበር።

