የኢትዮጵያ አየር መንገድ በግማሽ ዓመት ከ10 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች በማጓጓዝ 4.4 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት 6 ወራት 10.64 ሚሊየን መንገደኞችን በማጓጓዝ 4.4 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አስታውቋል።

ይህ አፈጻጸም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ14 በመቶ ዕድገት ያሳየ ሲሆን፣ ተቋሙ ካቀደው ግብም የ2 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተገልጿል።

የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ዛሬ የካቲት 3 ቀን 2018 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በግማሽ ዓመቱ ውስጥ ከመንገደኞች በተጨማሪ 451 ሺህ ቶን ንብረት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ማጓጓዝ መቻሉን አብራርተዋል።

አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹን ለማስፋት ባደረገው ጥረትም በቅርቡ ፖርቹጋል ፖርቶ፣ አቡዳቢ እና አንድ ተጨማሪ ከተማን በመጨመር አጠቃላይ የመዳረሻዎቹን ቁጥር ከ145 በላይ አድርሷል።

በሀገር ውስጥ በኩልም ያቤሎን በመጨመር የበረራ መዳረሻዎቹ 23 መድረሳቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል።

አየር መንገዱ የትራንስፖርት አቅሙን ለማሳደግ በወሰደው እርምጃ A350-1000 አውሮፕላንን ጨምሮ 7 አዳዲስ አውሮፕላኖችን ወደ ሥራ ያስገባ ሲሆን፣ በዚህም አጠቃላይ የአውሮፕላኖቹ ቁጥር 147 ደርሷል።

በሌላ በኩል የኢትዮዽያ አየር መንገድ የአሜሪካ መንግስት ከቪዛ እና ከጉዞ ገደብ ጋር በሚያወጣው ደንብ እና መመርያ ምክንያት፤ በረራዎችን እየቀነስኩ ነው አለ።

በዚህ የጉዞ ገደብ ምክንያት ፤ በአፍሪካ እና አካባቢው የደንበኞች ቁጥር እንደቀነሰበት ተናግሯል። ይህን ተከትሎም የመንገደኞች ቁጥር እየቀነሰበት መሆኑ ተጠቅሷል።

አየር መንገዱ የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀሙን አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ፤ አሁን ካሉኝ የተሻሉ አውሮፕላኖች ቢኖረኙ የተሻለ ፍጥነት እና እድገት ይኖረኛል ብሏል።

በአለም ላይ ያሉ ግጭቶች፤ የአየር ጠባይ እና ሌሎችም ችግሮች ስድስት ወሩን ሲፈተንበት እንደቆየ ሰምተናል።

የአውሮፕላን እጥረት ስላለብኝ ወደ ምፈልገው ቦታ ለመብረር አልቻልኩም ብሏል።

ትልልቅ እና ግዙፍ አውሮፕላኖች ቢኖሩኝ ኖሮ ወደ እሩቅ እና ወደ ምፈልገው ሐገር በቀጥታ እበር ነበርም ብሏል።

አየር መንገዱ በውጭ ሀገር ለሰጠሁት አገልግሎት የውጭ ምንዛሪ ለመሰብሰብ ተቸግሬያለሁ፤ በቀላሉ እየመነዘርኩ ለማውጣትም አልቻልኩም ብሏል።

አሁንም በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገሮች የውጭ ምንዛሪ ተይዞብናል ብሏል።

በብዙ ጥረት እና በተለያዩ የዲፕሎማሲ መንገዶች ለመሰብሰብ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስረድቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህን ሁሉ ፈተናዎች አልፎ በስድስት ወር ውስጥ 4 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ማግኘቱን ተናግሯል።
ይህም ከእቅዱ ሁለት በመቶ ጨምሯል ተብሏል።

ከባለፈው አመት ጋር ሲመሳከርም የ 14 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው ተናግረዋል።

ገቢው የተገኘው የአገልግሎት ዘርፋ በማደጉ እና አዳዲስ የበረራ መስመር እና ድግግሞሽ በመኖሩ እንደሆነ አቶ መስፍን ተናግረዋል።

አየር መንገዱ ሰባት አዳዲስ አውሮፕላን እንደተረከበም አስረድቷል።

የካፒታል በጀት ፕሮጀክት ተቀርፆም 300 ሚሊየን ዶላር ግድም ለፕሮጀክት አውያለሁ ብሏል።

በስድስት ወራቱ በቢሾፍቱ ለሚገነባው ግዙፍ አየር መንገድ በርካታ መሰረተ ልማቶች መጠናቀቃቸውን ሰምተናል።

አየር መንገዱ ቦታው ላይ ቤት ለነበራቸው አርሶ አደሮች ዘመናዊ ቤት አስረክቧል፤ ኑሯቸውም ምቹ እንዲሆን የቢዝነስ ከባቢ ፈጥረናል ተብሏል።

ከአዲሱ የአየር መንገዱ ፕሮጀክት ጋር በተገናኘ የመጀመርያው የመሬት ማደላደል ስራ መጀመሩንም ሰምተናል።

በጥቂት ወራት ውስጥ ተርሚናል ፤ የአውሮፕላን መንደርደሪያዎች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ስራ ይከናወናል ሲሉ ዋና ስራ አስፈጻሚው መስፍን ጣሰው ተናግረዋል። 35 አለም አቀፍ ኩባንያዎችም የዚህን መሰረተ ልማት ግንባታ ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል ተብሏል።

በመጪዎቹ አስር ቀናትም ፍላጎት ያላቸው ተለይተው የጨረታ ሂደት ይጀምራል ተብሏል።

የአውሮፕላን ማረፍያ ሙሉ ዲዛይን ተጠናቆ በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን ሰምተናል።

የአውሮፕላን ጥገና አቅም ለማሳደግ ማስፋፊያ ተሰርቷል ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው ፤ አዲስ ዋና መስሪያ ቤት ግንባታ እየተሰራ ነው፤ 42 በመቶ ደርሷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በስድስት ወራቱ 260 ሚሊየን ብር የሚያወጣ በጎ ስራ መፈፀሙንም ሰምተናል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe