በአዲስ አበባ ከተማ የወተት ምርት እና ስርጭት ደኅንነቱን ጠብቆ ለተጠቃሚዎች እንዲደርስ ለማድረግ ሁሉንም አምራቾች እንዲሁም አከፋፋዮች የሚያካትት አዲስ የሕግ ማዕቀፍ መዘጋጀቱ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ አርሶ አደር እና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዶክተር ፀጋ ለማ፣ “ከከብት እርባታ ጣቢያዎች እስከ ማከፋፈያ ሱቆች ድረስ ያለው የቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል” ብለዋል።
አክለውም፤ ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ 11 ክፍለ-ከተሞች ባለሙያዎችን በመመደብ ከአንድ ላም አርቢ ገበሬ እስከ ትላልቅ አከፋፋዮች ድረስ ተመሳሳይ የቁጥጥር መንገድ በመከተል ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የቁጥጥር ስራው ስፋት እና ሁኔታ እንደየተቋማቱ ቢለያይም ሁሉንም እንደሚያካትት የተናገሩት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ በተለይም ለሰፊው ማኅበረሰብ ምርት የሚያቀርቡ የወተት አምራቾች እና አከፋፋዮች ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ገልፀዋል።
በተጨማሪም፤ “አነስተኛ የወተት ማምረት እና ማከፋፈል ስራ ላይ የተሰማሩ አካላትን ጥራትና ደኅንነት ለማረጋገጥ፣ አምራቾቹ የሚጠቀሙባቸውን ቁሳቁሶች ደረጃቸውን በጠበቁ ቁሳቁሶች እንዲተኩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ ይሰራል” ብለዋል።
በአነስተኛ ደረጃ ላይ ያሉ አምራቾች ከግንዛቤ እጥረት እና ከቸልተኝነት የተነሳ የምርት ጥራት እና ደኅንነት እንዳይጎዳ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ እና ደረጃቸውን የጠበቁ ቁሳቁሶችን እንዲጠቀሙ የማድረግ ስራ እንደሚከናወንም ታውቋል።

