አንድ አዲስ ጥናት እንደሚያሳየው፣ የዓለም ሕዝብ ብዛት ምድር ያለ ጉዳት በዘላቂነት ልትሸከመው ከምትችለው መጠን አልፏል። ተመራማሪዎች ከ200 ዓመታት በላይ የቆዩ መረጃዎችን በመመርመር እንዳሰሉት፣ አሁን ባለን የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ምድር በምቹ ሁኔታ ልታስተናግደው የምትችለው የሕዝብ ብዛት 2.5 ቢሊዮን ብቻ ነው።
ቢበዛ እንኳን ልትሸከም የምትችለው ገደብ 12 ቢሊዮን ነው። ይሁን እንጂ አሁን ላይ የዓለም ሕዝብ 8.3 ቢሊዮን በመድረሱ፣ ምድር ከአቅሟ በላይ እየተሸከመች መሆኑን ጥናቱ አስጠንቅቋል።
የሕዝብ ዕድገት ፍጥነት ቀደም ሲል ከነበረው ቢቀንስም፣ አጠቃላይ የሰው ቁጥር ግን አሁንም እየጨመረ ነው። ይህ መጨመር የተፈጥሮ ሀብቶችን እያሟጠጠ፣ የውኃ እጥረትን እያባባሰ፣ እንስሳትና ዕፅዋት እንዲጠፉ እያደረገ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን እያባሰ ይገኛል። በኃይል አጠቃቀም፣ በመሬት አያያዝ እና በፍጆታ ባህላችን ላይ ፈጣን ለውጥ ካላደረግን፣ የዓለም ኢኮኖሚና የተፈጥሮ ሚዛን ከባድ አደጋ ውስጥ ሊወድቅ እንደሚችል ተገልጿል።
ምንም እንኳን የጥናቱ ውጤት አስደንጋጭ ቢሆንም፣ አሁንም ተስፋ እንዳለ ተመራማሪዎቹ ጠቁመዋል። ዓለም በጋራ ከተነሳች እና የተፈጥሮ ሀብቶችን በአግባቡ የምንጠቀምበትንና የምናከፋፍልበትን መንገድ ከቀየርን ችግሩን መቀነስ እንችላለን ብለዋል።
ግዮን ማለዳ

