የዓለም ቁጥር አንዱ ቱጃር ኢለን መስክ ግሪክ በሞት አፋፍ ላይ ትገኛለች አለ

ግሪክ በከባድ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች ተባለ፡፡ የዓለም ቁጥር አንዱ ቱጃር ኢለን መስክ ግሪክ በሞት አፋፍ ላይ ትገኛለች ብሏል፡፡

ባዶ መንደሮች፡ሰራተኛ አልባ ተቋማቶች እና ባዶ ትምህርት ቤቶች በግሪክ እየታዩ ነው ተብሏል፡፡ ግሪክ ከባድ የሚባለውን የኢኮኖሚ ቀውስ ካለፈች ዓመታት በኋላ በሌላ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች መባሉ ተሰምቷል፡፡ አሁን ግሪክ አዳዲስ በሚወለዱ ሰዎች ቁጥር መቀነስ ክፉኛ እየተፈተነች እንደደምትገኛ ታውቋል፡፡

የግሪክ የውልደት መጠን በ27 በመቶ እንደቀነሰም ተነግሯል፡፡ ግሪክ አሁን በቂ ህጻናት የሏትም የተባለ ሲሆን፤ኢለን መስክም ይህን ሁኔታ የግሪክ ሞት መቃረቡን አስረጂ ነው ብሏል፡፡ በግሪክ በትምህርት ቤት መማሪያ ክፍሎች ገብተው የሚማሩ ተማሪዎች ባለመወለዳቸውና ክፍሎቹም ኦና በመሆናቸው ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ እያስገደደ ነው፡፡

በዚህ የውልደት መጠን መቀነስ ምክንያትም እስካሁን በአገሪቱ ከ700 በላይ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸው ታውቋል፡፡ በ2022 ግሪክ ያስመዘገበችው ጠቅላላ የውልደት መጠን ከ77ሺ በታች ነበር፡፡ ይህ ደግሞ በክፍለ ዘመኑ ከተመዘገቡ ዝቅተኛ የውልደት መጠን ውስጥ የሚካተት እንደሆነ ተገልጻል፡፡

በ2023 በግሪክ የሞት ምጣኔው በ2022 ከነበረው የውልደት መጠን እጥፍ ሆኖ 140ሺ ነበረ፡፡ እንደ ግሪክ የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ከሆነ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች ቁጥር ባለፉት 7 ዓመታት ብቻ በመቶሺዎች ቀንሷል፡፡

ይህንን መሠረት አድርጎም ግሪክ ካሏት ትምህር ቤቶች ውስጥ ከ5 በመቶ በላይ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶቿን ለመዝጋት ተገዳለች፡፡

ጃፓንም ከግሪክ ጋር ተመሳሳይ ሁኔታ ገጥሟታል፡፡ በተለይም በገጠሩ አካባቢ ትምህርት ቤቶችን እየዘጋች ነው፡፡

በሌላ በኩል በዚህ ዓመት ደቡብ ኮሪያ 50 የሚደርሱ ትምህርት ቤቶችን መዝጋቷ ታውቋል፡፡ ሁሉም አገራት ወደዚህ ውሳኔ እንዲገቡ ያስገደዳቸው የውልደት ምጣኔ በጣም ማሽቆልቆሉ ነው፡፡ ኢለን መስክ ከሰሞኑ መላው አውሮፓ ሊጠፋ እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡

መስክ አውሮፓ የወሊድ ምጣኔን ካላሳደገች ልትጠፋ እንደምትችል ነው የገለጸው፡፡ መስክ የወሊድ ምጣኔ ማሽቆልቆል ከአየር ንብረት ለውጥ የበለጠ ለስልጣኔ አደጋ ነው ብሏል፡፡

ከኤዥያ እስከ አውሮፓ፡ከሰሜን እስከ ደቡብ አሜሪካ በዚህ ወቅት አገራት ከውልደት ምጣኔ መቀነስ ጋር ተያይዞ ከባድ ችግር ውስጥ ገብተዋል፡፡

እንደ መንግስታቱ ድርጅት መረጃ ከሆነ በዓለማችን አዲስ የሚወለዱ ህጻናት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ ነው፡፡ በጣም ጥቂት ህጻናት እየተወለዱ ነው ማለት፤ጥቂት የሚሰሩ ሰዎች ነው የሚኖሩት ማለት ነው፡፡ ይህ ሆነ ማለት ደግሞ የሰራተኛ እጥረት ይፈጠራል፤የኢኮኖሚ እድገትም ይዳከማል፡፡

የመንግስታቱ ድርጅት የውልደት መጠን እንዲቀንስ ካደረጉ ነገሮች ውስጥ የኑሮ ውድነት አንዱ እንደሆነ ጠቅሷል፡፡ እንደ ተቋሙ ገለጻ 39 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ልጅ ለማሳደግ የሚሆን በቂ ገንዘብ የላቸውም፡፡ 22 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ልጅ ወልዶ ለማሳደግ የሚሆን መኖሪያ ቤት የላቸውም፡፡ 18 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ለህጻናቱ የሚሆኑ እንክብካቤዎችን ለማድረግ የሚያስፈልጉ ቁሶችን ማሟላት የማይችሉ ናቸው፡፡ መንግስታት ይህንን ቀውስ ለመፍታት ልጅ ለሚወልዱ ሴቶች የተለያዩ ማበረታቻዎችን ይሰጣሉ፡፡ ይህም ሆኖ ግን በሚታሰበው መጠን ችግሩ ሊቀረፍ አልቻለም፡፡//

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe