አስመራን አያውቃትም፡፡ ስለ አስመራም ብዙ አልሰማም፡፡ ግን በልጅነት ዕድሜው እናቱ ጥላው ስትሄድ አማራጭ አጣ :: ሰፈሩን ፈራ:: የሚያውቃትን መርካቶ ጥሎ በምናቡ ወደ ሰሜናዊት ኮከብ ሸሸ:: በራዲዮ የሰማውን “አዝመሪና ” ሙዚቃ እያንጎራጎረ …!
ጌታቸው ካሳ “አዝመሪና” ልክፍት ሆናበት በኮልታፋ አንደበቱ ለዓመታት ያዚማት እንጂ ከእርሱ የልጅነት ቁመት የማይተናነሰው ቴፕም ለድምፃዊነቱ ባለውለታ ነበር:: በአፍላነቱ ዘመን የመርካቶው ኤልቪስ ይባል የነበረው ጌታቸው ቤታቸው ውስጥ ከነበረው ቴፕ ጋር በፍቅር የወደቀው ገና በለጋነቱ ነው:: ይሁንና አባቱ በድርጊቱ ደስ ስላልተሰኙ ቴፑን ደበቁበት::
እርሱ ግን እጅ አልሰጠም:: ሙዚቃን ፍለጋ ከቤቱ ወጣ፡፡ ገና በስምንት ዓመቱ መርካቶ በሚገኘው ካሊፎርኒያ ሻይ ቤት ደጃፍ ላይ ከየኔ ቢጤዎች ጋር እየተቀመጠ ሙዚቃን መስማት ቀጠለ:: ካሊፎርኒያ ለጌታቸው ካሳ የሙዚቃ መርከቡ ናት፡፡ የአባቱን ዛቻ አስረስታ የኋለኛ ትልቅ ድምፃዊነቱ ጋር የምታደርስ፡፡
ጌታቸው ካሊፎርኒያ ሻይ ቤት ደጃፍ ላይ እየተገኘ የእነ ኤልቪስን ሙዚቃ እየሰማ እነሱን ለመምሰል ሲሞክር አባቱ ደጋግመው ይሄ መንገድ አያዋጣህም ማለታቸው አልቀረም:: በኋላ እንደውም የሙዚቃ በሮቹን ሁሉ ጠረቃቅመው ስታንጎራጉር ብሰማህ ውርድ ከራሴ አሉት:: ፈራ:: ካለሙዚቃ መኖር የማይችል መሰለው:: ለጋሃርን የስደት መስኮት አደረጋት:: ከአባቱ ይልቅ ለሙዚቃ ሊኖር ለመንደሩ ጀርባውን ሰጥቶ ወደ ድሬዳዋ ተጎዘ፡፡
የበርሃዋ ንግስት የሙዚቃ መሸጋገሪያ ድልድዩ እንጂ ማረፊያው አልነበረችም፡፡ በዚህ የተነሳም የምሥራቋን የሙዚቃ ማእከል ናፍቆ ሐረር ገባ፡፡ ሐረር ጌታቸውን በምሥራቃዊ ሰጐን ኦርኬስትራዋ በኩል ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ወዳጆች ያስተዋወቀች ከተማ ናት፡፡ ጄነራል ሞገስ በየነ እና ጄነራል ጌታቸው ሺበሺ ይመሩት የነበረው የያኔው ምሥራቃዊ ሰጐን ኦርኬስትራ በጥበቡ በላቸው የግጥም ደራሲነት “እመኛለሁ” የተባለች ዜማን ለጌታቸው አበረከተ፡፡
የመርካቶው ኤልቪስ ራሱ ዜማ በደረሰላት “እመኛለሁ” ሙዚቃው የታላቅነት ጉዞውን ቢጀምርም በምሥራቃዊ ሰጐን ኦርኬስትራ ግን ሊቀጥል አልፈለገም፡፡ በዚህ ምክንያት የምሥራቅ ኢትዮጵያን የሙዚቃ እምብርት ተሰናብቶ ወደ አዲስ አበባ ዳግም ተመለሰ፡፡
“መጀመሪያም ባልመጣህ ከመጣህ ደግሞ ባልራቅከን!” ያሉት ሁለቱ ጀኔራሎች ግን መጥፋቱን የአንድ ድምፃዊ መጉደል ብቻ ያደረጉት አይመስልም፡፡ የታጠቀ አሰማርተው ከተደበቀባት አዲስ አበባ መለሱት፡፡ ይሁንና የመርካቶው ኤልቪስ ወታደር ልታደርጉኝ እንደሆነ ስለሰማሁ በዚህ መንደር ከዚህ በኋላ መኖር አልችልም ሲል እቅጩን ነገራቸው፡፡ ዓላማቸው የከሸፈባቸው ሁለቱ ጀነራሎችም በጌታቸው ላይ የጣሉት ተስፋ እንደጉም ተነነ፡፡ ምኞታቸው በአጭር እንደተቀጨ ሲገባቸውም መቆጣጠር አቆሙ፡፡
ጌታቸውም አላመንታም እንደገና ወደ ትውልድ ከተማው ተመልሶ “እመኛለሁን” ውቤ በርሃ ይዞ ገባ፡፡ በፓትሪስ ሉሙምባ ምሽት ክበብም ደመቀ፡፡ መነጣጠቅ በበዛበት በወቅቱ የአዲስ አበባ የምሽት ቤቶች እንቅስቃሴ ውስጥ ትኩረትን ለመሳብ የቻለው የመርካቶው ኤልቪስ በሶምብሬሮ የምሽት ክበብ ባለቤት አቶ ሥዩም ጥረት ፓትሪስ ሉሙምባን ለቅቆ ሰንጋ ተራ አካባቢ ወዳለው “ሶምብሬሮ ክበብ” አመራ፡፡
የአምስት ብር ደሞዝተኘነቱ አብቅቶም አሥራ አምስት ብር ይከፈለው ጀመር፡፡ ጌታቸው በ“ሶምብሬሮ” ቆይታው “ሳይሽ እሳሳለሁ” የተባለውን ዜማ በመድረስ በዕውቅናው ላይ ዕውቅና ጨመረ፡፡ ነገር ግን ለዝናው እርካብ በሆነው “ሶምብሬሮ” አልዘለቀም፡፡ ወደ አክሱም አዳራሽ ተዛወረ፡፡
በፖትሪስ ሉሙምባ የምሽት ክበብ ምርጥ ከበሮ ተጫዋች መሆኑን ያስመሰከረው የወቅቱ ታዳጊ በ“ሶምብረሮ” እና “አክሱም አዳራሽ”ም ፒያኖ መግረፍ ለመደ፡፡
ነገር ግን በእዚያ መንደርም በብዙ መቆየትን ስላልወደደ የአክሱም የምሽት ክበብ ሥራውን አቋርጦ ወደ ፒያሳ አቀና፡፡ “ቬነስ የምሽት ክበብ” ጋር ተቀላቅሎም በበርካታ ዜማዎች መድመቁን ቀጠለ፡፡ የመርካቶው ብላቴና ከቬነስ ባንድ ጋር “ምን ይሆን ምስጢሩ” እና “ፍቅርሽን እሻለሁ” የተሰኙ ሙዘቃዎችን ለአድማጭ አቀረበ፡፡ በቬነስ የምሽት ክበብ ተደናቂነትን ያተረፈው ወጣቱ አቀንቃኝ እንደገና ወደ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ፊቱን አዞረ፡፡
በዚህ ቆይታውም በ“ዘ–ሸበሌስ” እና በ“ዋልያስ ባንድ” አጃቢነት የተለያዩ ሸክላዎችን ለማሳተም ቻለ፡፡ በ1964 የወጣው በተለምዶ “ፈጣኑ ትዝታ” እየተሰኘ የሚጠራ ሙዚቃውም የአገሩን ልማድ ሽሮ የትዝታን አጨዋወት ከእንጉርጉሮ አላቆ ለውዝዋዜ ሲያበቃ ጌታቸው በከተማው ስሙ ናኘ፡፡ ረጋ ያለ የትዝታ ዘፈኑም የኢትዮጵያ ራዲዮ የሙዚቃ ምርጫ ፕሮግራምን ተቆጣጠረ::
ይህ አጋጣሚ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ተጨማሪ አሳታሚ እንዲመጣ መነሳሳትን መፍጠሩ አልቀረም፡፡ የከሊፋ ሪከርድስ ባለቤቱ አሊ ከሊፋ ጌታቸውን ወደው አሳታሚነቱን አንድ አሉ:: ብዙ ሳይቆዩም የወደዱትን ሰው ዜማ ለማሳተም በቁ:: “ዋልያስ ባንድ” ያጀባቸው “ዝማም ሰው ለበኔ”፣ “አልተገናኘንም” “የኔ ዓለም” እና “ወደድኩህ ማለትሽ ላይቀር” የተሰኙት ሙዚቃዎችም ዝናን አተረፉ፡፡
ከ1973 የዋልያስ ባንድ የባሕር ማዶ ጉዞ በኋላ በአሜሪካ የስደት ሕይወትን የመረጠው ጌታቸው ካሳ በባይተዋርነት ዘመኑም ተወዳጅ አልበምን ለአድማጭ አድርሷል፡፡ በ“ኢትዮ ስታር ባንድ” አጃቢነት በኢትዮጵያ ቀረጻው የተካሄደው ይህ ድንቅ አልበም የዘመን አቧራ ያልሸፈናቸውን “እወድሻለሁ“: “ትዝ ባለኝ ጊዜ“:”የከረመ ፍቅር“: “አገሬን አትንኳት” እና የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናው አብዝተው ከሚወዷቸው ሙዚቃዎች አንዱ የሆነውን “አትጥፊ ከጎኔ” የያዘ ነው::
ጌታቸው ሲነሳ ሁለት ጉዳዮች ተደጋግመው መታወሳቸው የሚቀር አይመስልም:: ቀዳሚው ስለ ኢትዮጵያ የተጫወታቸው “ቀና ብዬ ሳዬው” እና “አገሬን አትንኳት” የተሰኙት timeless classic ስራዎቹ ናቸው::
ሌላው የአባቱ ስም ጉዳይ ነው:: ከአዲስ አበባ ኮብልሎ ለሙዚቃ ሲል ሐረር የገባው የያኔው ጌታቸው ጸጋዬ ምስራቃዊ ሰጎንን ከተቀላቀለ በኋላ ሁለት ነገሮች ከፊቱ ተደቀኑ፡፡
ሙዚቃን ማቆም አልያም ራሱን ለአደጋ አጋልጦ በድምፃዊነቱ መቀጠል፡፡ የወቅቱ የፍቅር ጓደኛው አሰገደች ካሳ መፍትሄ ግን ከሁለቱም ውጭ ነበር::
“ለምን የእኔን አባት ስም አትጠቀምም?” አለችው፡፡
አለመነታም፡፡
ለሙዚቃ ሲል አባቱን ረሳ፡፡ ጸጋዬን አውጥቶ ካሳ የሚለውን ተካ–ጌታቸው ካሳ!
ጌታቸው ዓለምን የገጠማት ብቻውን ይመስለኛል:: በእርሱ መንገድ ውስጥ የእናትና አባት ፍቅር እንዲሁም የቤተሰብ መውደድ ቅንጦት ነበሩ:: የፍቅር ግንኙነቱም ቢሆን ፍፃሜው አላማረም:: እናም ለጋራ የምትከብደውን ዓለም ለብቻው ሊጋፈጥ ከፊቷ ቆመ:: ግን ስንት ዓመት ዓለምን መግጠም ይቻላል? ስንት ማዕልትስ ሞትን አሳፍሮ ይኖራል ?
የጠዋት ፀሐይ ጨረር በዳምናው ዘልቆ
ትኩስ ፍም በመምሰል ሲታይ አሸብርቆ
መንፈስን ያድሳል : ግን ይህንን አይተን
ውበትም ይጠፋል ደመናው ሲበተን
(ውበትም ይረግፋል ከተሰኘ ሥራው ላይ የተወሰደ)
#ሞትን ያሳደደው ጌታ–ቸው ካሳ! ( ከመኩሪያ ጌታቸው ገፅ የተገኘ)

