የዓመቱ ዜና እረፍት አቶ ተስፋዬ ዳባ “የኢትዮጵያ መጻህፍት ድርጅት” ባለቤት

የዘርፈ ብዙ ሙያ ባለቤት የሆኑት እና በተለይም በኢትዮጵያ ዘመናዊ ህትመት ላይ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱት አቶ ተስፋዬ ዳባ ዮዶ ባደረባቸዉ ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተዉ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።

አቶ ተስፋዬ ከአባታቸዉ ዳባ ዮዶ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ አለሚቱ ይደታ የካቲት 24 ቀን 1931 ዓ.ም በወለጋ ክፍለ ሀገር ተወለዱ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በትውልድ አካባቢውያቸው በሚገኘዉ ጊምቢ ሚሲዮን ት/ቤት ፤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው በቀድሞ ስሙ ባላባት በአሁኑ መጠሪያው መድሐኒያለም ት/ቤት ተከታትለዋል።

አቶ ተስፋዬ በ1952 ዓ.ም ሀገራችን ኢትዮጵያዊ በቀረበላት ጥሪ መሰረት ከሌሎች ሀገራት ጋር በመሆን በተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ሀይል ስር በመሆን ከዘመተው የቃኘዉ ሻለቃ ጦር ጋር ወደ ኮንጎ ዘምተዉ ግዳጃቸዉን በጀግንነት በመፈጸም የመቶ አለቅነት ማዕረግ ሲሰጣቸው በንጉሰ ነገስቱም ተሸልመዋል።

ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዉም በወቅቱ “voice of Ethiopia” (የኢትዮጵያ ድምፅ ) በመባል ይታወቅ በነበረው የእንግሊዘኛ ቋንቋ ጋዜጣ ላይ በረዳት አዘጋጅነት ለሁለት ዓመት አገልግለዋል።

አቶ ተስፋዬ በወቅቱ በትምህርት ሚንስትር እና በታዋቂው የእንግሊዝ ሀገር ኦክስፎርድ ዩንቨርሲቲ ፕሬስ መካከል በነበረው ስምምነት የትምህርት እድል አግኝተው በኦክስፎርድ ዩንቨርሲቲ በመጻህፍት ህትመት አዘጋጅነት ላይ ስልጠና የወሰዱ ሲሆን ዩንቨርሲቲው ባመቻቸላቸው እድልም በኬንያ ተቀጥረው አገልግለዋል። ከዚያም ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ በኢትዮጵያ ቅርንጫፍ መክፈቱን ተከትሎ በስራ አስኪያጅነት የመስራት እድል አግኝተዋል።

በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጁ ዘመናዊ የመማሪያ መጽሀፍትን አትመዉ ለአንባቢያን በማቅረብ የሚታወቁት እኚህ ታላቅ ሰው ከሌሎች ምሁራን ጋር በመተባበር “የጥበብ ማሀደር” በተሰኘው እንቅስቃሴ “የተማረ ሁሉ ያስተምር “ የሚል መርህ በመያዝ በተለይም በሀገራችን የገጠሩ ክፍል የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማስተማር ትልቅ ስራ ሰርተዋል ።

የደርግ መንግስት ስልጣን በያዘ ጊዜ የውጭ ሀገር ተቋማትን በመውረሱ በስራ አስኪያጅነት ሲያገለግሉበት የነበረው የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ ቅርንጫፍ ቢዘጋም አቶ ተስፋዬ “የኢትዮጵያ መጻህፍት ድርጅት” ብለው የሰየሙትን አሳታሚ ድርጅት በራሳቸው አቋቋሙ። በድርጅቱ አማካኝነትም የብዙ ዕውቅ እና ታላላቅ ደራሲያን ስራ ለህዝብ እንዲደርስ በህትመቱ ዘርፍ ከፍተኛ ሚና ተጫወቱ።

ከነዚህም ውስጥ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን ፣ በዓሉ ግርማ፣ ብርሃኑ ዘሪሁን እና ማሞ ውድነህ ጥቂቶቹ ናቸው። ከእውቁ ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ ጋር የቀረበ ወዳጅነት የነበራቸው አቶ ተስፋዬ ከደራሲው የመጨረሻ ስራ ማለትም ኦሮማይ ውጪ ያሉትን ሁሉንም መጽሓፍት በማተምና ለአንባቢያን በማቅረብ ትልቅ ድርሻ ነበራቸው።

ደራሲ በዓሉ ግርማ የመጨረሻው መጽሐፋ የሆነው ኦሮማይን በሚያሳትምበት ወቅት በነበረው የደርግ መንግሥት ጥርስ ሊያስነክስብት እንደሚችል አልፎም ለህይወቱ ጭምር አስጊ መሆኑን በመጥቀስና ለሃገራችን ብዙ እንድትሰራ ታስፈልጋታለህ በማለት እንዳያሳትም ተደጋጋሚ ግፊት ያደርጉበት እንደነበር በተለያዩ ጊዜያት የተናገሩት አቶ ተስፋዬ በመጨረሻ የመጽሐፉ ለህትመት መብቃት በ1976 ዓ.ም. ለደራሲው ሕይወት መጥፋት መንስኤ ሊሆን ስለመብቃቱ እምነት ነበራቸው።

በተጨማሪም በደርግ መንግስት በነበረው የእድገት በህብረት ዘመቻ ላይ ለትምህርቱ የሚውሉ መጽሀፍትን በማተም በዘመቻው የራሳቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

አቶ ተስፋዬ የባላገሩ ቴሌቪዥን አድቫይዘሪ ቦርድ አባል በመሆንም አገልግለዋል።ለልጆቻቸውና ለቤተሰቦቻቸው ባላቸው ልዩ ፍቅር የሚታወቁት አቶ ተስፋዬ በዚህ እድሜያቸውም ቢሆን በተለይም አንዱ ልጃቸው የገጠመውን የማይሽር ህመም ሲያስታምሙ ቆይተዋል።ይህም ሁኔታ በራሳቸው ጤና ላይ ጭምር ተጽእኖ ፈጥሮ ባደረባቸው ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ86 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።

አቶ ተስፋዬ የአምስት ልጆች አባትና የአምስት የልጅ ልጆች አያት ነበሩ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe