“ብዙም ትውስታ የለኝም” በሚላት ይርጋለም ነው ውልደቱ፤ መጋቢት 5 1957 ዓ.ም። የውልደት አመቱ ከሀገሪቱ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ የምስረታ ዓመት ጋር መግጠሙን አስተውሎ ‘ይህ ልጅ የሚዲያ ሰው ይሆናል‘ ያለ ባይኖርም፤ እርሱ ግን በኋለኛው ዘመኑ በህትመቱም በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው ላይ ስፖርትና ታሪክን ይዞ መግነን ችሏል።
ከማያስታውሳት ይርጋለም ከተማ የበዛ የልጅነት ጊዜውን ወዳሳለፈባት ሻሸመኔ አቀና። በዚያ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ተከታትሏል፤ የእግር ኳስና የጽሑፍ ችሎታውን ፈልጎ አግኝቷል። በአፄ ናዖድ ተማሪ ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን እየተከታተለ የቡና ነጋዴ አባቱ ገቢ ወጫቸውን ሲፅፉበት ከርመው የሞላ መዝገባቸውን ይሰጡታል፤ ህፃኑ ገነነ ተቀብሎ ከጋዜጦች የሚያገኘውን የስፖርተኞችን ፎቶ እየለጠፈ ለጓደኞቹ ያከራያል። ግማሹን የሚያዩ የቁልፍ(አዝራር) ፣ ሙሉውን የሚኮመኩሙ 5 ሳንቲም እንዲከፍሉ ግድ ይላቸው ነበር።
እዚያው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለ አዲስ ዘመንንና ሰለሞን ተሰማ ያዘጋጅ የነበረው “ስፖርት ፋና” ጋዜጦችን ያዞራል። 10 ጋዜጣ ለማዞሩ የሚከፈለውን 10 ሳንቲም ከመቀበል ይልቅ አንድ ጋዜጣ ተቀብሎ ይሄዳል። ከጋዜጦቹ ላይ የሚያገኛቸውን ስዕሎች ከአባቱ የሞላ መዝገብ ላይ እየለጠፈ፤ ዜናዎቹን በራሱ መንገድ ድጋሜ እየፃፈ ገቢውንም የጽሑፍ ችሎታውንም እኩል አሳደገ።
ጋዜጣ ከማሳደድ ጎን ለጎን ኳስ ሊያድን “አረንቻታ” ለተባለ የሰፈሩ ቡድን በግብ ጠባቂነት ተሰለፈ። “ጎል ውስጥ መቀመጥ ስለማልወድ እየወጣሁ ብዙ ጎል ይገባብኝ ነበር” የሚለው ገነነ ከአረንቻታ ቀጥሎ “ነበልባል” ለተባለ ቡድንም በግብ ጠባቂነት ተጫውቷል።
7ኛ ክፍል ሲደርስ የወቅቱ መንግስት ከቀይ ሽብር በኋላ ወጣቱን በስፖርት ለመያዝ አልሞ በርካታ ውድድሮችን ያደርጋል። በቴኒስና በዝላይ ተሳትፎ ሳይቀናው የማታ ማታ አስር ሺ ሜትር ተወዳድሮ በወንድሙ እገዛ አንደኛ ወጥቶ ባልዲ እንደተሸለመ ያስታውሳል። ይህ በሆነ በዓመቱ ከሰፈር ጓደኞቹ ጋር በመሆን “ቀዩ እምቡጥ” በሚባል የውትድርና ምልመላ ፕሮግራም ሰልጥሎ ለምደባ በዝግጅት ላይ እያለ የሻሸመኔ ቡድን የግብ ጠባቂ እጥረት ስላለበት የካምፑ ኃላፊና የወረዳው የስፖርት ሊቀመንበር “ገነነ ጥርሱ ቦንብ መንከስ አይችልም” ብሎ ሲያስቀረው ያለቀሰውን ለቅሶ ዛሬም አይረሳ።
እርሱ ብቻ ሳይሆን 5ቱም ወንድሞቹ እግር ኳስ ይጫወታሉ። አንድ ቡድን ውስጥ በዝተው ስላሉ የቀበሌያቸው ቡድን 09 ከመባል ይልቅ ‹የአቶ መኩሪያ ቡድን› ነበር የሚባለው። ገነነ ከሁሉም ወንድሞቹ በልዩነት ለሲ ቡድን አጥቂ፣ ለቢ ቡድን አማካኝ፣ ለኤ ቡድን ግብ ጠባቂ ሁኖ በመጫወቱ ሁለገብ ተጫዋች ተብሎ ብርሌ ተሸልሟል።
የሸገር መንታ መንገዶች
1974 ዓ.ም ከግብ ጠባቂነቱ በመውጣት የሜዳ ተጫዋች በመሆን አውራ ጎዳና ለተባለ ቡድን ከፍተኛ ተከፋይ ሁኖ በ50 ብር ተቀጠረ። በአውራጃዎች ውድድር የሻሸመኔን መለያ ለብሷል፤ የሸዋ ውድድር ላይ ደግሞ ሃይቆችና ቡታጅራን ወክሎ ድንቅ ብቃቱን ናዝሬት ላይ አሳይቷል። ይህ ድንቅ ብቃቱ በ1975 ዓ.ም ገና የ12ኛ ክፍል ተማሪ እያለ ለሜታ ቢራ እንዲፈርም አድርጎት ወደ ሸገር እንዲዘልቅ ሁኗል። ከሚከፈለው 183 ብር ላይ ቤት ተከራይቶ፣ የምግብ ኮንትራት ይዞ፣ ተግባረ– ዕድ ለትምህርት ከፍሎ የተረፈውን ቆጥቧል። 125 ብር በቆጠበበት ዓመት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ “ምርጥ ቆጣቢ” ብሎ እንደሸለመው እያስታወሰ በቅርቡ መንገድ ላይ ያገኘው የባንኩ ወጣት ሰራተኛ “አካውንት ክፈት” ሲለው “አንተ ሳትወለድ የባንኩ ደንበኛ ነበርኩ” እንዳለው ይናገራል።
እግር ኳሱን እየተጫወተ፣ ከተግባረ ዕድ በጄነራል መካኒክነት ተመርቆ ለሜታ ቢራ እየሰራ ለአዲስ ዘመን ፅሑፍ መፃፍ ጀመረ። በእጁም በእግሩም የሚታትር ትጉህ ሆነ። በ1978 የነበረ ዓለም ዋንጫ ላይ ማራዶና በእጁ ጎል ሲያገባ የገነነ ጽሑፍ ደሞ ከእድሜ እኩያው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በፀጋ ቁምላቸው በኩል ገባ። ስሙ በቴሌቭዥን ሲጠራ የሰሙት አለቃው ስራውን አመቻችተውለት ቤተ መጽሐፍት እየገባ መፃፉን አበረታ። ለተለያዩ ጋዜጦችና ሚዲያዎች ቢፅፍም ከየካቲት መጽሔት በስተቀር አይከፍሉትም ነበር። እርሱ ግን ሁለት የሚወዳቸው ነገሮች ስለከፈሉት ደስተኛ ነው፦ እግር ኳስና የጽሑፍ ስራው።
የሜታ ቢራ ተጫዋች ሁኖ 3 ጊዜ የኢትዮጵያ ሻምፒዮን የነበረ ቢሆንም በ1978 ዓ.ም የብር ሜዳልያ ተሸላሚ የሆነበትን የፍፃሜ ጨዋታ ግን አይረሳም። ከህንፃ ኮንስትራክሽን ጋር በነበረ የፍፃሜ ግጥሚያ ገነነ ለአጋሩ ግብ ጠባቂ አቀብላለሁ ያላት ኳስ ራሱ መረብ ላይ አርፋ አንድ ለዜሮ በሆነ ውጤት ተሸንፈው ዋንጫውን አጥተዋል። ታሪክ ወዳጁ ገነነ ይሄን የራሱን ገጠመኝ እያሰበ “በታሪክ ብቸኛው ሰው ነኝ… አሸናፊው ቡድን የተጋጣሚው ተጫዋች አግብቶለት ዋንጫ ሲበላ የመጀመሪያው ነው” ይላል። ይሄኛውን ጎል ጨምሮ በዓመቱ ውስጥ አምስት ጊዜ ራሱ ላይ ማግባቱን በማስታወስ “ራሴ ላይ የማገባው የጎል ድርቅ ሲኖር ነው… እዚያ ማግባት ካልቻልክ እዚህ ታገባለህ” ይላል በቀልድ መልክ።
ተወዳጁ ጋዜጠኛ ገገነ መኩሪያ (ሊብሮ) የራሱነ አሻራ አኑሮ በደንገተኛ ህመም ለአዳር በያዘው አልቤረጎ ውስጥ ህይውቱ አልፎ ነው የተገኘው፡፡
(ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን )

