ጋዜጠኛ አሰፋው ገረመው በቀድሞ ሸዋ ክ/ሀገር በጮቦና ጉራጌ አውራጃ በወሊሶ አካባቢ ከአባታቸው ከአቶ ገረመው ብርመጂ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ቦጋለች ታልጋ ህዳር 3 ቀን 1951 ዓ/ም ተወለደ።
በወሊሶ ከተማ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለ ሲሆን ከአ/አ ዩኒቨርስቲ በቋንቋ እና ስነ–ፅሁፍ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቋል።
ጋዜጠኛ አስፋው ገረመው ከየካቲት 1974 አስከ ግንቦት 1975 ዓ/ም ድረስ በአየር ጤና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በመምህርነት ያገለገለ ሲሆን በኮንትራት ቅጥርም በምስራች ድምጽ አለም አለም አቀፍ አገልግሎት በጋዜጠኝነት ለተወሰነ ጊዜ ሰርቷል ፡፡
ከዚያም በኃላ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ኢትዮጵያ ሬዲዮ ከመጋቢት 3 ቀን 1977 ዓ/ም ጀምሮ በቋሚነት በጡረታ እስከ ተሰናበተበት ህዳር 30 ቀን 2011 ዓ/ም ድረስ ሞያው በሚጠይቀው መደብ በረዳት አዘጋጅነት ፤ በአዘጋጅነት ፤ በአርታኢነትና እንዲሁም ከም/ዋና አዘጋጅነት ጀምሮ በተለያዩ የሃላፊነት ደረጃዎች አገልግሏል። በአስመራ የኢትዮጵያ ሬዲዮም ሙያዊ ኃላፊነቱን ተወጥቶ ስርአት ሲቀየርም በስደት ያሳለፈው ህይወቱ መራር ነበር ፡፡
ጋዜጠኛ አስፋው ገረመው ሞያውን ለማዳበር በሀገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ አጫጭር ስልጠናዎች ላይ የተሳተፈ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በተለያየ ጊዜ ባካሄዳቸው የዜናና ፕሮግራም አቀራረብ ለውጦች ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የአድማጭ ተመልካች እርካታ እንዲፈጠር ደከመኝ ታከተኝ ሳይል ሰርቷል ፡፡
ጋዜጠኛ አስፋው ገረመው በኢትዮጵያ ሬዲዮ ዘመን የማይሽራቸው ፕሮግራሞች በማዘጋጀትና በማቅረብ ይታወቃል ፡፡
ከአድማስ ባሻገር፣ ኢትዮጵያን እንቃኛት ፤ የኪነጥበባት ምሽት የተሰኙ ተወዳጅ ፕሮገግራሞችን እና ሌሎችም በማዘጋጀት እና በማቅረብ በአድማጮች ዘንድ በጣም ተወዳጅ የነበረ ጋዜጠኛ ነበር ፡፡
ጋዜጠኛ አስፋው ገረመው የኢትዮጵያ ሬዲዮ ጣቢያ መክፈቻና የተለያዩ ፕሮግራሞች መለያ ቲምን በመረዋ ድምፁ በማዘጋጀት ይታወቃል ፡፡ አሁን ድረስም እየተላለፉ ይገኛሉ ፡፡
አስፋው ገረመው ለሞያው በነበረው ከፍተኛ ፍቅር ጀማሪ ጋዜጠኞችን ወደ ሞያው ጠልቀው እንዲገቡ በማሰልጠንና እየተከታተለ ሞያዊ ሂስ በመስጠት ጋዜጠኞች ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዲ ደርሱ የተጫወተው ሚና ከፍተኛ ነበር ።
ከግል ህይወቱ በላይ ዕድሜውን ሙሉ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ሙያውን ወድዶና አክብሮ ሲያገለግል የቆየው ጋዜጠኛ አስፋው ገረመው በተወለደ በ 65 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል ፡
ጋዜጠኛ አስፋው ገረመው የሁለት ልጆች አባት ነበር ፡፡“ይህ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ነው” የሚለውን ድምፅ ጀምሮ አሁንም ድረስ አየር ላይ የሚገኙ ስራዎች ያሉት ተወዳጅ ጋዜጠኛ ነበር።ጋዜጠኛ አስፋው ኢትዮጵያን እንቃኛት፣ ከአድማስ ባሻገር፣ የሬዲዮ መዝናኛ፣ ዜና፣ ኪነ–ጥበባት፣ ቅዳሜ መዝናኛ እና የመሳሰሉ ዝግጅቶች ላይ ደማቅ አሻራ አሳርፏል።
ኅዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት የተለየው አስፋው በቀጨኔ መድኃኒዓለም መካነ–መቃብር የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ተፈጽማል፡፡

