አንጋፋውና የአረብኛ ቋንቋ ‘ታብሎይድ ‘አገር አቀፍ ጋዜጣ “ ዓልዓለም “ ዋና አዘጋጅ የነበረው ፣ ጋዜጠኛ እዮብ ግደይ ከዚህ ዓለም በሞት የመለየቱን ዜና የተሰማው በዚህ አመት ነው ።
እዮብ በተለይ ከ2005_ 2009 መጨረሻ ደግሞ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የማኔጅመንት ኮሜቴና የኤዲቶሪያል ፎረም አባል በመሆን አገልግሏል ። እዮብ በአረቡ አለምና የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ውስጥ እየተዶለተ ያለውን ሴራ ቀድሞ የሚረዳበት ተሰጥኦ ነበረው ። አረብኛና ትግሬኛ እንደአማርኛ የሚገለግልባቸው ቋንቋዎች ነበሩ ።
እነ ሱዳን ትሪቡን፣ አልሃራምና ካይሮ ቲቪን … የመሰሉ ሚዲያዎችንም በየእለቱ የሚከታተላቸው የስራ መነሻዎቹ ነበሩ። በርካታ የሱዳንና ግብፅ ጋዜጠኞች ጓደኞችም ነበሩት ። እናም ካይሮና ካርቱም የተባለውን ብቻ ሳይሆን፥ የታሳበውን በመተንተን ለኤዲቶሪያል ኮሚቴው በማቅረብ ይታወቅ ነበር ።
እነዚህን ተጨባጭ እውነታዎች ለመተግበር የረዳው ደግሞ በሱዳን ካርቱም ማደጉና የአገሩን ባህል ጠንቅቆ ማወቁም ነው ። እዮብ ከአገሩና ከብሄራዊው ጥቅም ውጭ “ የግል ፣ የቡድንና የሃይማኖት ተከታዬ ጥቅም “ የሚለው ዝባዝንኬ ያልተጫነበት ባለሙያ ነበር።
እዬብ በተለይ የህዳሴ ግድብ መሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት እለት ጀምሮ በሚያዘጋጃቸው ጋዜጦችና በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለአረቡ አለም የኢትዮጵያን ጥቅምና ክብር የሚገልፁ ፅሁፎችና ለድህረ ገፅ የሚስማሙ መረጃዎችን እያሰነዳ በማቅረብም ይታወቃል ።
የሱዳንና ግብፅ የህትመት ውጤቶችን በመፈተሽ የመልስ ምት እንዲሰናዳ አቅጣጫ የሚያመላክተውም እሱ ነበር ። ከፕሬስ ድርጅትም አልፎ ለመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉ/ሚ/ር አንዳንድ የአረብኛ ቋንቋ የህትመት ውጤቶች የአርትኦት ድጋፍ ያደርግ ነበር፡፡
ከዚያም አልፎ በአዲስ አበባ ከሚገኙ የአረቡ አለም ኢምባሲዎች ጋር መልካም ግንኙነት በመፍጠር ኢፕድ ልዮልዮ ድጋፎችን እንዲያገኝ ይሰራ ነበር ። እዮብ በተለይም ለሙያው ያለው ፍቅርና ክብር ላቅ ያለ በመሆኑ፣ የአገሩን ጥቅምና ክብር የሚያስጠብቁ ልዩ ልዩ ጽሁፎችን በአረቡ ዓለም ጋዜጦች እና ድረገጾች ሳይቀር ማሳተም የቻለ አንጋፋ ጋዜጠኛ ነበር።

