የኢትዮጽያ መገናኛ ብዙሃን ም/ቤት የጋዜጠኞች ሙያ ማረጋገጫ መታወቂያን ለመስጠት እንቅስቃሴ የጀመርኩት ከባለስልጣኑ ጋር ከተነጋገርኩ ወዲህ ነው አለ፡፡
የኢትዮጽያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ለጋዜጠኞች የሙያ ብቃት ማረጋገጫ መታወቂያ መስጠት እና የጋዜጠኞችን ምዝገባ ማከናወን ም/ቤቱ ስልጣን የለውም የሚል መግለጫ በትላንናው እለት አውጥቷል፡፡
የም/ቤቱ ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ ታምራት ኃይሉ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረት የሙያ ማረጋገጫ መታወቂያ ለአባላቶቻችን ለመስጠት ነው እየሰራን ያለነው፤ ይህም አክቲቪዝምንና ጋዜጠኝነትን ለመለየት ያግዛል፤ ወደ እንቅስቃሴው ከመግባታችን በፊትም ከባለስልጣኑ ጋር ውይይት አድርገናል ብለዋል፡፡
የብቃት ማረጋገጫ መታወቂያው ተደባልቆ የሚገኘውን የጋዜጠኝነት እና የአክቲቪዝም ስራ ለመለየት እንዲሁም ጋዜጠኞች በሚሰሯቸው ዘገባዎች ስህተት እንኳን ሲፈጠር ወደ እስር እንዳይወሰዱ እና ጉዳያቸውም በስነ ምግባር ደንብ እንዲታይ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል፡፡
በሌሎች ሀገራትም ያለው ልምድ ይህ መሆኑን ከተለያዩ ሀገራት የሚዲያ አካላት ጋር በመገናኘት ልምድ መወሰዱም ተነግሯል፡፡
የኢትዮጽያ መገናኛ ብዙሃን ም/ቤት የጋዜጠኞች የሙያ ማረጋገጫ መታወቂያ፡የጋዜጠኞች ምዝገባ እንዲሁም ብሔራዊ የሚዲያ ሽልማት ለማዘጋጀት መጋቢት 9 ያስጠናውን ጥናት ለውይይት ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

