የፕሮፌሰር ኤልሳቤጥ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሀንስ የቀብር ሥነ ስርዓት ተፈጸመ

“በአዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዋና ዳይሬክተር በመሆን ያገለገሉት እና በበርካታ የአደባባይ ምሁራዊ አስተዋጿቸው የሚታወቁት ፕሮፌሰር ኤልሳቤጥ ወልደጊዮርጊስ በተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ሻርጃ ከተማ በሚገኘው በአፍሪካ ኢንስቲትዩት ግሎባል ስተዲስ ዮኒቨርሲቲ በፕሮፌሠርነት እና ዲፓርትመንት ሀላፊነት እያገለገሉ ሳለ በአደረባቸው ህመም እሁድ መጋቢት 7 ቀን 2017 ዓም ህይወታቸው ማለፋ ይታወቃል።

የፕሮፌሰር ኤልሳቤጥ የቀብር ሥነ ስርዓት አርብ መጋቢት 12 ቀን 2017 ዓ.ም በመንበረ ጸባኦት በቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ተከናውናል።

ፕሮፌሰር ኤልሳቤጥ ወልደጊዮርጊስ ከእናታቸወ ወ/ሮ ዋካ ድንቄ እና ከአባታቸው ብላታ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ ግንቦት 1 ቀን 1948 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ተወለዱ።
ከአምስት ወንድሞቻቸው እና አንዲት እህታቸው ጋር በአዲስ አበባ ያደጉትና የቤተሰቡ የመጨረሻ ልጅ የሆኑት ኤልሳቤጥ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በናዝሬት ት/ቤት ተምረዋል።
በከፍተኛ ትምህርት ደግሞ በአሜሪካ ሞርጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚከስ ትምህርት ተከታትለው በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀዋል። በዚህ ሙያቸውም እዚያው አሜሪካ በተለያዩ ባንኮች አገልግለዋል።
በተለይ ለሥነ-ጥበብ እና ለታሪክ በነበራቸው ልዩ ዝንባሌ እንዲሁም እስክንድር ቦጎስያንን ከመሳሰሉ ሰዓሊዎች እና የጥበቡ ማኅህበረሰብ ጋር በነበራቸው የጠበቀ ወዳጅነት ወደ ጥበቡ ዓለም በመሳባቸው፤ ማስተርሳቸውን በሙዚየም ጥናት ከኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ፣ ዶክትሬታቸውን ደግሞ በሥነ-ጥበብ ታሪክ እና ሂስ ከኮርኔል ዩኒቨርሲቲ በ2000 ዓ.ም አግኝተዋል።
የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥነ-ጥበብ ታሪክ ላይ በማተኮር ለዶክትሬት መመረቂያ ያካሄዱት ጥናት እና ምርምር እና ያዘጋጁት የመመረቂያ ጽሑፍ በ2011 ዓ.ም ‘Modernist Art in Ethiopia’ በሚል ርዕስ ለታተመው መጽሐፋቸው ዋነኛው እርሾ ነበር።
ይህ በኦሃዮ ዩኒቨርሲቲ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትብብር ለህትመት የበቃው መፅሐፍ በርካታ አንባቢ ያተረፈና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናና ሽልማት የተቸረው ሰነድ ለመሆን በቅቷል።
ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር ተቋምን የመምራት ኃላፊነት ተረክበው ከ1996 እስከ 2002 ዓ.ም በዳይሬክተርነት አገልግለዋል።
በዚህ የኃላፊነት ዘመናቸው የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የዳርፉርን ጉዳይ ጨምሮ ወሳኝ በሆኑ ዓለም እና ሀገር አቀፋዊ አጀንዳዎች ዙሪያ ጉባኤዎችን እንዲያሰናዳ አስችለዋል።
ተቋሙ ከዚያ ቀደም የነበረውን የረዥም ጊዜ ልምድ እና እውቀት መሰረት በማድረግ ይበልጥ እንዲደራጅ እንዲሁም ክብሩን እና የዕውቀት ሃብቱን እንዲያሳድግ ጉልህ ድርሻ አበርክተዋል።
በመቀጠልም በዩኒቨርሲቲው የቴአትር ጥበባት ማዕከል፣ የያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት እና የአለ ሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት ተቀናጅተው “እስክንድር ቦጎስያን የክወና እና የዕይታ ጥበባት ኮሌጅ” እንዲቋቋም በማስቻል ኮሌጁ ከተመሰረተበት ከ2001 እስከ 2004 ዓ.ም በዲንነት አገልግለዋል።
በተጨማሪም በአለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት የፊልም እና የሥነ-ጥበብ ድኅረ ምረቃ ትምህርት ክፍልን በማቋቋም ሂደት የበኩላቸውን ሚና ተጫውተዋል። በዚሁ ትምህርት ክፍል በማስተማር የተማሪዎቻቸው የሥነ-ጥበብ እሳቤ፣ ዕውቀት እና ልምምድ እንዲዳብር የነበራቸው አስተዋጽኦ ከልዩ ሙያዊ አበርክቶዎቻቸው አንዱ ሲሆን፣ ይህንኑ ተግባራቸውን አሁን በተለያዩ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ የቀድሞ ተማሪዎቻቸው በኩራት የሚመሰከሩት ዕውነት ነው።
ፕሮፌሰር ኤልሳቤጥ ለሀገሪቱ ብቸኛ የሆነው የዘመናዊ ሥነ-ጥበብ ቤተ-መዘክር ገብረ ክርስቶስ ደስታ ማዕከል መስራቾች መካከልም አንዷ ናቸው። ቤተ-መዘክሩ ከተቋቋመበት ከመስከረም 2001 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ዙሮች ሁለት ጊዜ በዳይሬክተርነት መርተውታል። በዚሁ ወቅት እንደተለመደው በርካታ ትዕይንቶችንም አዘጋጅተውበታል። ከእነዚህም መካከል በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ዕውቅና ያካበቱትን የትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ጁሊ ምህረቱን እና ዴንማርካዊ አይስላንዳዊውን አላፉር ኤልያሰንን ጨምሮ የስመ ጥር ሰዓልያን ሥራዎችን ጭምር ለህዝብ ዕይታ አቅርበዋል።
ፕሮፌሰር ኤልሣቤጥ ዘመናዊነት በኢትዮጵያ፣ ዘመናዊ ሥነ-ጥበብ እና ከተሜነትን ጨምሮ በተለያዩ ማህበረሰብ ተኮር ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ሲምፖዝየሞች፣ ኮንፍረንሶች እና ውይይቶችን አዘጋጅተዋል።
ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የባህል አምባ እየሆነች በመጣቸው በተባበሩት ዐረብ ኢምሬትስ የሻርዣ ከተማ በሚገኘው ዓለም ዐቀፍ ጥናት ዩኒቨርሲቲ (Global Studies University) የአፍሪካ ኢንስቲትዩት የአሊ መዝሩዊ ቀዳሚ ከፍተኛ ፌሎ በመሆን ተቀላቅለዋል።
በተቋሙ የድኅረ ምረቃ እና የዶክትሬት ትምህርት ክፍል ምሥረታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሲሆን፤ በተጓዳኝ የሂውማኒቲስ ትምህርት ክፍልን በመምራት፤ ካሪኩለም በመቅረፅና በማስተማር አዲስ ለተከፈቱት የትምህርት መርሐ-ግብሮች አገልግሎት ሰጥተዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe