በኢትዮጽያ ነዋሪ ያልሆነ ሰው በአገር ውስጥ መረጃዎችን በማሰራጨት በሚያገኘው ገቢ ላይ ግብር ሊጣልበት ነው፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው የገቢ ግብር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ በኢትዮጽያ ነዋሪ ያልሆነ ሰው በአገር ውስጥ የዲጂታል መረጃዎችን በማሰራጨት ያገኘው ገቢ በአገር ውስጥ እንደተገኘ ተደርጎ ሊጣልበት እንደሆነ ተገልጻል፡፡
በማሻሻያ ረቂቅ አዋ ከዲጅታል ይዘት ፈጠራ የሚገኝ ገቢን በተመለከተ የተደነገገው አንቀጽ 29 አንድ ግለሰብ ወይም ድርጅት ከቪዲዮ ማጋሪያ አገልግሎቶች፡ከማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች፡ከድምጽ ማስተላለፊያ ፖድካስት አገልግሎቶችና የቀጥታ ስርጭት መድረኮች ከሚገኙ ገቢዎች ዓመታዊ ግብር እንዲከፍል ግዴታ ይጥልበታል፡፡
በኦንላይን መድረኮች ዲጂታል ይዘት በመፍጠርና በማሰራጨት የሚገኝ ማንኛውም ገንዘብ ወይም ገንዘብ ነክ ያልሆነ ገቢ ግብር የሚከፈልበት እንደሆነ ያብራራል፡፡
ማስታወቂያዎችና ስፖንሰርሺፖች፡የምርት ስምምነቶችና ድጋፎች፡የአጋርነት ግብይትና የምርት ምደባዎች የደጋፊዎች አስተዋጾ፡የገንዘብ ስጦታዎች ወይም የብዙሃን የገንዘብ ማሰባሰብ ክራውድ ፈንዲንግ የዲጂታል ወይም የአካላዊ ሸቀጦች ሽያጭ ለማስታወቂያ እንቅስቃሴ የተገኙ ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶችና ተመሳሳይነት ያላቸው ሌሎች ክፍያዎች ከዲጂታል ይዘት ፈጠራ የሚገኝ ገቢ በሚል ግብር ይጣልባቸዋል ተብሏል፡፡
በረቂቅ አዋጁ ላይ በኢትዮጽያ ነዋሪ ያልሆነ ሰው በኢትዮጽያ ውስጥ መረጃዎችን በኬብል፡በሬዲዮ፡በኦፕቲካል ፋይበር፡በቴሌቪዥን ማሰራጫ፡በአነስተኛ ማሰራጫ ተርሚናል፡በኢንተርኔት ሳተላይት በማሰራጨት የሚገኘው ገቢ መረጃው የመነጫው ከኢትዮጽያ ቢሆንም ባይሆንም በኢትዮጽያ የተገኘ ገቢ እንደሆነ ተደርጎ እንደሚቆጠር ተደንግጓል፡፡
በስራ ላይ ባለው አዋጅ ከኢትዮጽያ ውስጥ ያልመነጨ ማንኛውም ገቢ የውጭ አገር ገቢ በሚል ተደንግጎ ቆይቷል፡፡
በረቂቅ አዋጁ የታክስ ባለስልጣን በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ዝርዝረዘቸውን አድራሻቸውን ለግብር ዓላማ ለማግኘት የሚያስችል ስርዓት እንደሚያቋቁም ተደንግጓል፡፡
ረቂቅ አዋጁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ወይም ኢትዮጽያ ውስጥ በሚገኝ የውጭ አገር ኤምባሲ፡ዲፕሎማሲያዊ ሚሲዮን ወይም ሌላ የቆንስላ ተቋም ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞችን የሚመለከት መረጃ የመሰብሰብ ሃላፊነት ተጥሎበታል፡፡
ሚኒስቴሩ ይህንን መረጃ ለታክስ ባለስልጣኑ የማስተላለፍ ሃላፊነት ይኖርበታልም ተብሏል፡፡

