ዳሸን ባንክ ለውድ ደንበኞቹ እንደ ዋስትና ሠነድ፤ ዕንቁ፤ የከበሩ ድንጋዮችን ጨምሮ ሌሎች ውድ ዋጋ ያላቸውን የከበሩ ንብረቶችን የማስቀመጥ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡
የዳሸን ባንክ ትሬዠሪ ማኔጅመንት መምሪያ ዳይሬክተር አቶ አንዱዓለም በለጠ እንደተናገሩት፣ ዘመኑ ባፈራቸው የደህንነት መሳሪያዎች ተደራጅቶ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የዳሸን ባንክ የውድ ንብረቶች ማስቀመጥ አገልግሎት በተለያየ ጊዜ በደንበኞች የቀረቡ ጥያቄዎችን ለመመለስ የቀረበ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በተለይም የማዕድን ዘርፉ ላይ ለተሰማሩ የባንኩ ደንበኞች ታቅዶ የቀረበው ይህ አገልግሎት ደንበኞች እንደፍላጎታቸው ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ሳጥን ወይም ካዝናዎችን ከባንኩ በመከራየት እንደ ወርቅ፣የከበሩ ማዕድናት፣ፓስፖርት፣የጋብቻ ሰርተፊኬቶች ሌሎች ውድ የሆኑ ንብረቶችን የሚያስቀምጡበት እንደሆነ አቶ አንዱዓለም ተናግረዋል፡፡
የግለሰብ ደንበኞችም ሆኑ ተቋማት በዳሸን ባንክ ቅርንጫፎችና ዲስትሪክቶች ቀርበው አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ ሲጨርሱ ወደ ዋና መሥሪያ ቤት ቀርበው አገልግሎቱን ማግኘት የሚችሉ ሲሆን፣ የዚህ አገልግሎት ደንበኞች ለዚሁ የሚሆን ልዩ መታወቂያ ይዘጋጃላቸዋል፡፡
ለደንበኞች አዲስ አገልግሎት ከማቅረብ ባሻገር ባንኩ ከዚህ አመታዊ የኪራይ ገቢ አንደሚያገኝ፣ ሌሎች ደንበኞችን ለማፍራት እንደሚያስችለው የተናገሩት አቶ አንዱዓለም፣ ነገር ግን ትልቁ ነገር ዳሸን ባንክ የደንበኞቹ ንብረቶች ደህንነት አስተማማኝ እንዲሆን የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት መቻሉ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
የደንበኞች ፍላጎትን ያማከሉ አገልግሎቶችን በማቅረብ የሚታወቀው ዳሸን ባንክ ደህንነቱ በከፍተኛ ሁኔታ በሚጠበቀው የዳሸን ባንክ የከበሩ ንብረቶች የማስቀመጥ አገልግሎት ደንበኞች እንዲገለገሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ሱፐርአፕን ጨምሮ አዳዲስ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ ግንባር ቀደም የሆነው ዳሸን ባንክ፣ በቀጣይም የደንበኞቹን ፍላጎት ለማሟላት ተጨማሪ ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን ለክቡራን ደንበኞቹ በቅርቡ የሚያስተዋውቅ ይሆናል፡፡
ዳሸን ባንክ የከበሩ ንብረቶችን የማስቀመጥ አገልግሎት ጀመረ

