ዳሽን ቢራ የኢትዮጵያ ኪነጥበብ ባለሙያዎች በጎ አድራጎት ማህበር “የክብር አምባሳደር” ሆኖ ተሾመ
የ5 አንጋፋ አርቲስቶች ሲኖሩባቸው የነበሩ የጭቃ ቤቶች ወደ ዘመናዊ መኖሪያነት ተቀይረዋል፣
የኢትዮጵያ ኪነጥበብ ባለሙያዎች በጎ አድራጎት ማህበር ላለፉት ዓመታት ለጥበብ ባለሙያዎች ሲያደርግ የቆየውን ድጋፍ በማጠናከር፣ ዳሽን ቢራ ፋብሪካን የማህበሩ “የክብር አምባሳደር” አድርጎ ሾመ።
ሹመቱ የተሰጠው ፋብሪካው የአንጋፋ አርቲስቶችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ላሳየው ቀዳሚ ተሳትፎና ለዘርፉ ላበረከተው አስተዋጽኦ እውቅና ለመስጠት ነው።
ማህበሩ የሀገር ባለውለታ የሆኑ ከ200 በላይ የኪነጥበብ ባለሙያዎችን የጭቃ ቤቶች ወደ ዘመናዊ መኖሪያነት ለመቀየር በነደፈው እቅድ መሰረት፣ ዳሽን ቢራ ፋብሪካ የፕሮጀክቱ ግንባር ቀደም ተባባሪ በመሆን ስራውን ጀምሯል። የ2018 ዓ.ም የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግም፦የ5 አንጋፋ አርቲስቶችን አርቲስት ችሎታው ከልካይ፣ አርቲስት ሽመላሽ ለጋስ፤ አርቲስት ጻጋይ ዘርፉ የጭቃ ቤቶች ሙሉ ወጪውን በመሸፈን ወደ ዘመናዊ መኖሪያነት ቀይሯል።
አርቲስቶቹ ቀሪ ዘመናቸውን በደስታና በክብር እንዲያሳልፉ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል።
የክብር አምባሳደርነት የሹመት ሰርተፍኬቱን የዳሽን ቢራ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ማቲያስ ጌታቸው ከማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ ከክቡር ዶክተር ዳዊት ይፍሩና ከደራሲና ሃያሲ ክቡር ዶክተር አያልነህ ሙላት እጅ ተቀብለዋል። ይህ አጋርነት በችግር ውስጥ ለሚገኙ የጥበብ ሰዎች ትልቅ ተስፋን የፈነጠቀ መሆኑ በስነ-ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።
የማህበሩ ፕሬዝዳንትና የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ ፕሮሞተርና የሚዲያ ባለሙያ ልዑል ጌታነህ ከተማ እንደገለጹት፣ ማህበሩ ላለፉት 16 ዓመታት ባለሙያዎችን በህክምናና በኑሮ ሲረዳ ቢቆይም፣ የአንጋፋ አርቲስቶች የመኖሪያ ቤት ሁኔታ “አንገት የሚያስደፋ” ነበር። ዳሽን ቢራ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የወሰደው እርምጃ በኪነጥበቡ ማህበረሰብ ዘንድ ትልቅ አክብሮት አስገኝቶለታል።
በምርቃቱ ስነ-ስርዓት ላይ የታደሙ ታላላቅ የኪነጥበብ ሰዎች፣ የተከናወነው ተግባር ለሌሎችም ባለሙያዎች የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀ መሆኑን ገልጸው ለተቋሙ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ማህበሩ ዳሽን ቢራ ለኪነጥበቡ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አስተላልፏል።
#ድሬቲዩብ
ዳሽን ቢራ የ5 አንጋፋ አርቲስቶች የጭቃ ቤቶች ወደ ዘመናዊ መኖሪያነት ቀየረ

