የተወለደችው በጎንደር፣ ደራ ፎገራ አውራጃ፣ ልዩ ስሟ ሀሙሲት በምትባል አነስተኛ መንደር ነው። በቤተሰቦቿ የሥራ ዝውውር ምክንያት ለአጭር ጊዜ አሰላ ከዛም አዲስ አበባ ኖራለች። በትምህርቷ በጣም ጎበዝ (ቀለም) ከሚባሉት ተማሪዎች ተርታ የምትመደብ ተማሪ ነበረች። ለሙዚቃ በነበራት ከፍተኛ ፍቅርና ፍላጎት ድምፃዊ ለመሆን ወደ ፖሊስ ኦርኬስትራ በመሄድ ያደረገችው የመጀመሪያ ሙከራ “ድምፃዊ መሆን አትችይም” በሚል መራር ውሳኔ ተደመደመ። እንደማስተዛዘኛ ግን በተወዛዋዠነት እድሏን እንድትሞክር ተፈቅዶላት ፖሊስ ኦርኬስትራን ለ7ወር በተወዛዋዥነት በነፃ በማገልገል ኪነጥበብን ተቀላቀለች።
ከ7 ወር ግልጋሎት በኋላም በነፃ ዝውውር ወደ አንጋፋው የሀገር ፍቅር ቲያትርቤት በመዘዋወር ከ1965 እስከ 1967 ዓ.ም በተወዛዋዠነት አገለገለች። በዚህ እልህ አስጨራሽና ተስፋ አስቆራጭ ሂደት ሙያዋን የጀመረችው አይበገሬዋ ድምፃዊት የመጀመሪያ የሙዚቃ ሸክላዋን በተመለከተ አሳታሚው የታንጎ ሙዚቃ ቤት ባለቤት ባንድ ወቅት እንዲህ በሚል ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። “አስቴርን በሸክላ ለማስቀረፅ ስመርጣት ድምጿ አይሰማም ከሚል ስጋት “ይቅርብህ” ያሉኝ ሰዎች ብዙ ነበሩ። እኔ ግን ቁጥር 1 ስራዋን በድፍረት አሳትሜ አወጣሁት። ያው እንደተፈራውም ተቀባይነቱ ቀዝቃዛ ነበረ። ሰዎችን ስጠይቃቸው “ድምጿ ጥሩ ነው ምን እንደምትል ግን አይሰማም “ይሉኝ ነበር። እናም አስቴርም በወቅቱ “በቃ እኔ ሙዚቃ አይሆንልኝም” ብላ ተስፋ ቆረጠች። እኔ ግን እሷ ትልቅ ቦታ የምትደርስ ድምፃዊ እንደምትሆን እርግጠኛ ስለሆንኩኝ እልህ ውስጥ ገብቼ አስቴርንም አበረታትቼ ፣ የድርሰት ማጥኛ ቤት አዘጋጅቼ ፤ ውብሸት ፍሰሀን ጨምሬ ረጅም ጊዜ በፈጀ ጥናት በባህል መሳሪያዎች የታጀበ ስራቸውን አሳትሜ አወጣው። ተቀባይነቱ ዳር ከዳር ከመሆኑም በላይ ያኔ ያልተደመጠው የመጀመሪያ ስራዋ ሁሉ እንደገና እንደ አዲስ ይፈለግና ይሰማ ጀመር። ሀገሩ ሁሉ አስቴር ይል ጀመር።” በማለት ያስታውሰዋል ኘሮዲውሰር አሊ አብደላ፤ የታንጎ ሙዚቃ ቤት ባለቤት።
በዚህ መልኩ የአይበገሬነት ጉዞዋን የጀመረችው አስቴር አወቀ ግማሽ ክፍለን ዘመን በሚጠጋው የሙዚቃ ዘመኗ … አንድ የሸክላ ሙዚቃና 25 የሙዚቃ ካሴቶችን በግሏ፣ አንድ የሙዚቃ ካሴት ከድምፃዊ ውብሸት ፍስሀ ጋር በጋራ፣ ከድምፃዊ አለማየሁ እሸቴ ጋር” መች እንዲህ “የተሰኘ አንድ ዜማ በቅብብል፣ “እንኖራለን ገና” በሚል በኤች አይ ቪ ዙሪያ የተሰራ የጋራ አልበም፣ ለሚሊንየም የተጫወተችው ነጠላ ዜማ፣ የኛ ከተባሉ የሙዚቃ ቡድኖች ጋር በጋራ አንድ ዜማ ተጫውታለች። አስቴር በስራዋ የሀገሯን ሰዎች ብቻ ሳይሆን የውጭ ሀገር ሰዎችን ጆሮዎችም የሳበች ሲሆን ከሲቢኤስ (CBS) ኮርፖሬሽን ጋር የሰባት አመት ኮንትራት እንደነበራት ተገልፇል። በተመሳሳይም ከሌላ ከእንግሊዝ ሀገር ካምፓኒ ጋር ሌላ ኮንትራት ተዋውላ ስራዎቿን አበርክታለች። በታዋቂው ታይም (TIME) መፅሄት ላይ አዲስ አይነት የሙዚቃ ስልት ዘርፍ ትልቅ አድናቆት እና ክብር ተሰጥቷታል። ከዚህም ባሻገር “ካቡ” የተሰኘው አልበሟ በፈረንጆች አቆጣጠር በ1990 በ “CMJ New Music Charts” ላይ ለአራት ሳምንታት ከፍተኛ ቦታ (Top Position) ላይ እንዲሁም በ “Billboard’s World Music Charts” ላይ ለአስር ሳምንታት (Top Ten of Billboard’s World Music Charts) ላይ ቆይቷል።
አስቴር ወደ ኢትዮጵያ መጥታ ትልልቅ የሙዚቃ ዝግጅቶችን በጃንሜዳ፣ አዲስ አበባ ስታድየም፣ ሸራተን አዲስ እና ሚሊኒየም አዳራሽ አድርጋለች። ከዚህ ባሻገር በተደጋጋሚ እየደረሰ ያለውን የረሃብ አደጋ ሰለባዎች ለመርዳት በተደረገው ጥረት ወደ ሃገሯ በመምጣት በሙያዋ አስተዋፅኦ አበርክታለች። የራስሽን ዘፈን ስትሰሚ ምን ይሠማሻል ተብላ ተጠይቃ “ተለዋዋጭ ነው፣ በወጣትነት ጊዜዬ በጣም አፍር ነበር፤ የኔን ዘፈን ካዘፈንሽ ያንቺ መኪና ውስጥ አልገባም ነበር፣ የኔን ዘፈን ካዘፈንሽ እቤትሽ አልመጣም ነበር። ምክንያቱን ሁሌም በሰማሁ ቁጥር ይህን እንዲህ ማድረግ ነበረብኝ የምላቸው ስሜቶች ይሰሙኝ ነበር።” ብላለች። አስቴር ራሷን “አስቴር አወቀ በጣም ደግ፣ ስስ ቆዳ ያላት እና ትልቅ ለመሆን የምትፈልግ ሴት ናት። መፈቀርም ማፍቀርም የምትፈልግ ናት። ሌላ ትርጉም ሊሰጣት አይገባም ከተፈቀረች ይበቃታል። ሌላ ነገር አትፈልግም” ብላ ትገልፃታለች። አስቴር አወቀ አንድ ሴት ልጅ ያላት ሲሆን የግል ህይወቷን ከሰው ሸሸግ አድርጋ የምትኖር እና ከአደባባይ ይልቅ የግል ሰው እንደሆነች፣ ትልቅ የመድረክ ፍርሃት እንዳለባትም ትናገራለች። ባለድንቅ ተሰጥኦዋ እና እንደ ህፃን ልጅ የቅን ልብ ባለቤቷ አስቴር አወቀ
- የዜማ ደራሲ
- የግጥም ደራሲ
- በቅንብር የምትሳተፍ
- የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋች በተጨማሪም ኑሮዋን በአሜሪካን ሀገር ካደረገች ጀምሮ ደግሞ የተዋጣላት ዲዛይነር በመሆን ለረጅም አመት የሀገሯን ባህል አስተዋውቃለች። መድረክ ላይ የምታደርጋቸው ውብ የባህል ልብሶች በራሷ ዲዛይን የተደረጉ ናቸው።

