ኢንጂኒየር ኤፍሬም ጌታቸው የጃምቦ ሪል ስቴት ባለድርሻ ሆነ!
ጃምቦ ሪል ስቴት ግሩፕ ተወዳጁን ጋዜጠኛ ደረጀ ሃይሌን ለሦስት ዓመታት የሚቆይ የድርጅቱ የብራንድ አምባሳደር አድርጎ ዛሬ ሰኔ 19 ቀን 2017 ዓ.ም በሂልተን ሆቴል ሾመ።
የጃምቦ ሪል ስቴት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደበበ ሰይፉ በመርሐግብሩ ላይ እንደገለጹት፣ ጋዜጠኛ ደረጀ ሀይሌ የመጀመሪያውን የሥራ እንቅስቃሴውን በቅርቡ በሚካሄደው የሰሜን አሜሪካን የኢትዮጵያውያን የስፖርት ፌስቲቫል ላይ ጃምቦ ሪል ስቴት ግሩፕን በመወከል እንደሚጀምር ገልጸው ይህንን ተወዳጅ ጋዜጠኛ የብራንድ አምባሳደር አድርገን መሾማችን ትክክለኛ መሆኑን ከሰሞኑን ከማህበረሰቡ ምላሽ ተረድተናል በዚህም ደስተኞች ነነን ብለዋል።

የጃምቦ ሪል ስቴት ግሩፕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም ጌታቸው፣ ጋዜጠኛ ደረጀ ሃይሌን ወደ ቤተሰባቸው በመቀበላቸው ደስታቸውን ገልጸዋል። አቶ ኤፍሬም፣ ጋዜጠኛ ደረጀ ሃይሌ ባለው ሰፊ ልምድ፣ እውቅና እና ህዝባዊ ተቀባይነት ለጃምቦ ሪል ስቴት ብራንድ ግንባታ እና የድርጅቱን ዕድገት በማፋጠን ረገድ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት እምነታቸውን ገልጸዋል።
ጋዜጠኛ ደረጀ ሃይሌ በቅርቡ በሰሜን አሜሪካ በሚካሄደው የኢትዮጵያውያን የስፖርት ፌስቲቫል ላይ ጃምቦ ሪል ስቴት ግሩፕን ወክሎ የመጀመሪያውን የሥራ እንቅስቃሴውን እንደሚጀምር ታውቋል። ይህ ትልቅ ዓለም አቀፍ መድረክ ለጃምቦ ሪል ስቴት ዓለም አቀፍ እውቅናን ለማግኘት ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል።
በስምምነቱ መሠረት፣ ጋዜጠኛ ደረጀ ሃይሌ በአፍሪካ ህብረት አቅራቢያ ከሚገኘው የጃምቦ ሪል ስቴት ግንባታ ሳይት ውስጥ ባለ ሶስት መኝታ ቤት አፓርታማ እንደተሰጠው ተገልጿል። ይህ ደረጀ ሃይሌ የጃምቦን ምርቶች ጥራት በተግባር እንዲለማመድ እና በባለቤትነት ስሜት ለብራንዱ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ያስችለዋል ተብሎ ይታመናል።
ጃምቦ ሪል ስቴት ግሩፕ ከ29 ዓመታት በፊት በወንድማማቾቹ አቶ ደበበ ሰይፉ እና አቶ ወንድራድ ሰይፉ አማካኝነት “ጃምቦ ኮንስትራክሽን” በሚል ስያሜ እንደተቋቋመ ይታወቃል። ድርጅቱ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በግንባታ ዘርፍ ከፍተኛ ልምድ በማካበት እና በርካታ ታዋቂ ፕሮጀክቶችን በማከናወን በኢትዮጵያ የሪል ስቴት ገበያ ውስጥ ግንባር ቀደም ተዋናይ ሆኖ ቆይቷል።
ላለፉት 20 አመታት በልዩ ልዩ የሃላፊነት ደረጃዎች ላይ የሰራው የጃምቦ ሪል ስቴት ግሩፕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም ጌታቸው የረጅም ጊዜ አገልግሎቱንና ትጋቱን ምክንያት በማድረግ የድርጅቱ ባለቤቶች ወንድማማቾቹ አቶ ደበበ ሰይፉ እና አቶ ወንድራድ ሰይፉ አቶ ኤፍሬምን ሶስተኛው የድርጅቱ ባለድርሻ ማድረጋችውን ይፋ አድርገዋል፡፡

