ግብፅ ተጨማሪ 24 የራፋል ተዋጊ ጄቶችን ከ #ፈረንሳይ ለመግዛት ጥያቄ ማቅረቧ ተሰማ

​ግብፅ በፈረንሳይ የተሠሩ የራፋል (Rafale) ተዋጊ ጄቶች ስብስብን ለማስፋፋት እርምጃ መውሰዷን እና ዳሶ አቪዬሽን (Dassault Aviation) ለተሰኘው አምራች ኩባንያ ተጨማሪ 24 ጄቶችን ለመግዛት የሚያስችላትን የቴክኒክ ጥያቄ ማቅረቧን የፈረንሳዩ «ላ ትሪቡን» ጋዜጣ ዘገበ።
​ነሐሴ 26 ቀን 2018 ዓ.ም. የወጣው ዘገባ እንደሚያመለክተው፣ ይህ ጥያቄ ዳሶ አቪዬሽን ለግዥው የሚያስፈልጉ የቴክኒክ እና የንግድ ፕሮፖዛሎችን እንዲያቀርብ የሚጠይቅ እንጂ እስካሁን የተፈረመ የውል ስምምነት ወይም የጸደቀ ትዕዛዝ አይደለም። ዳሶ አቪዬሽን ለጋዜጣው አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።
​ግብፅ እ.ኤ.አ. በ2015 የመጀመሪያዎቹን 24 ተዋጊ ጄቶች፣ በመቀጠልም እ.ኤ.አ. በ2021 ሁለተኛውን የ31 ጄቶች ግዥ መፈጸሟን ተከተሎ፣ በአሁኑ ወቅት 54 የራፋል ተዋጊ ጄቶች በትዕዛዝ እና በስራ ላይ ይገኛሉ። ይህ አዲስ የውሳኔ ሃሳብ ወደ ውል ከተቀየረ የሀገሪቱ የራፋል ጄቶች ቁጥር ወደ 78 ከፍ የሚል ሲሆን፣ ይህም ግብፅን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የራፋል ጄቶች ከሚጠቀሙ ሀገራት ተርታ ያሰልፋታል።
​ጋዜጣው እንደዘገበው ይህ እርምጃ የተወሰደው ሀገሪቱ ካጋጠማት የፋይናንስ እጥረት ጋር ተያይዞ በወታደራዊ ግዥዎቿ ላይ እገዳ አድርጋ ከቆየችበት ጊዜ በኋላ ነው። በተጨማሪም እርምጃው ካይሮ በ1980ዎቹ እና 1990ዎቹ የተቀበለቻቸውን እና አገልግሎት ላይ የሚገኙ ከ200 በላይ አሮጌ የኤፍ-16 (F-16) ተዋጊ ጄቶቿን በአዲሶች ለመተካት እና ለማዘመን ለረጅም ጊዜ የገጠማትን ተግዳሮት ተከትሎ የተወሰደ ነው።
​ይህ ሊደረግ የታሰበው የራፋል ጄት ግዥ ከተሳካ፣ አሮጌዎቹን የውጊያ አውሮፕላኖች በመተካት የግብፅን የአየር ኃይል የበላይነት እና አቅም ለማስጠበቅ የሚደረገው ሰፊ ጥረት አካል እንደሚሆን ይገመታል።
​ወታደራዊ ተንታኞች እንደሚገምቱት፣ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2018 ዓ.ም. በሚካሄደው ሁለተኛው የአል አላሜይን ዓለም አቀፍ የኤሮስፔስ ኤግዚቢሽን ላይ ካይሮ የጦር አውሮፕላኖቿን ስብስብ ለማደስ ያላትን ቀጣይ አቅጣጫ የሚያመላክቱ ተጨማሪ መረጃዎች ሊወጡ ይችላሉ።
​ለዳሶ አቪዬሽን ኩባንያ ተጨማሪው የግብፅ ትዕዛዝ ቀደም ሲል በግብፅ፣ በካታር እና በተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ያከናወናቸውን ዋና ዋና ሽያጮች በማጠናከር፣ የራፋል ተዋጊ ጄት በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ጠንካራ ቦታ ይበልጥ የሚያጠናክርለት ይሆናል።//

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe