የአሸናፊዎች የቁጠባ ሒሳብ / Champions Saving Account በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለሚሳተፉ የእግር ኳስ ክለቦችና ደጋፊዎቻቸው የተዘጋጀ የቁጠባ ሒሳብ ሲሆን ስምምነቱ የተፈፀመው ፀሐይ ባንክ የአሸናፊዎች የቁጠባ ሒሳብ ማስጀመሪያ መርሐግብርን በዛሬው ዕለት ባካሔደበት ወቅት ነው።
ፀሐይ ባንክ የአሸናፊዎች የቁጠባ ሒሳብን ለማስጀመር በመጀመሪያ ምዕራፍ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ጋር ስምምነት አድርጓል።
የመግባቢያ ስምምነቱን የፀሐይ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ያሬድ መስፍን እና የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ፕሬዝዳንት አቶ አብነት ገብረመስቀል ተፈራርመዋል፡፡
በስምምነቱ መርሃ ግብር ላይ የፀሐይ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ያሬድ መስፍን ባደረጉት ንግግር የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች በፀሐይ ባንክ የአሸናፊዎች የቁጠባ ሒሳብ በመክፈት ሲቆጥቡ ከባንኩ ከሚያገኙት የተቀማጭ ወለድ አንድ በመቶ ለክለቡ ገቢ የሚደረግ ሲሆን የክለቡ ደጋፊዎች የአሸናፊዎች የቁጠባ ሒሳብ ሲከፍቱ ከተከፈተው ሒሳብ ተቀናሽ የሚደረግ የተወሰነ ብር ወዲያውኑ ለክለቡ የሚተላለፍ ይሆናል፡፡ ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በየአመቱ በ10 በመቶ የሚያድግ የአምስት ሚሊዮን ብር የስፖንሰርሺፕ ገቢ ከፀሐይ ባንክ ለክለቡ ገቢ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡
ለቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ የልምምድ ቦታ ግንባታ የሚውል እሰከ 40 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የረጅም ጊዜ ብድር የተመቻቸ መሆኑንም የፀሐይ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ያሬድ መስፍን ተናግረዋል፡፡

ጽሃይ ባንክ

ፀሐይ ባንክ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ኢንዱስትሪን ለማገዝ እና ውጤታማነቱን ለማረጋገጥ የሻምፒዮን/የአሸናፊዎች የቁጠባ ሒሳብ ይዞ መምጣቱን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡
በስምምነቱ መፈፀም ደስታቸውን የገለፁት የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ፕሬዝዳንት አቶ አብነት ገብረመስቀል፤ ስምምነቱ ለአምስት ዓመታት የሚቆይ አጋርነት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ስምምነቱ ለሁለቱም ተቋማት በርካታ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ያነሱት አቶ አብነት፤ ፀሐይ ባንክ በክለቡ የማህበራዊ ገፆች፣ ጋዜጣ፣ ሳምንታዊ የሬዲዮ መሰናዶ እንዲሁም በተለያዩ የግንኙነት መንገዶች አገልገሎቶቹን የማስተወዋወቅ ዕድል እንደሚኖረውም አረጋግጠዋል፡፡
ስምምነቱ ለጊዮርጊስ ደጋፊዎች የሚኖረው ተጫማሪ ፋይዳ፦
– የክለቡ ደጋፊዎች የአባልነት ክፍያቸውን በፀሐይ ባንክ በኩል እንዲከፍሉ ይደረጋል፣
– ለክለቡ ተጫዋቾችም ሆነ ሰራተኞች ወርሃዊ ደምወዝ በፀሐይ ባንክ በኩል ይከፈላል፣
– በባንኩ የሚያንቀሳቅሱት ገንዘብ ባደገ ቁጥር ባንኩ ድጋፋ እያደገ ይሄዳል ።
– የስታዲየም መግቢያ ቲኬቶች እና የክለቡ ቲሸርተና አልባሳት በፀሐይ ባንክ ቅርንጫፎች እንዲሸጥ ይደረጋል፣
– የክለቡ የተለያዩ የገቢ ማስገኛና ክፍያዎች ሁሉ በፀሐይ ባንክ በኩል የሚፈፀም ሲሆን ይህም ክለቡንም ባንኩም የበለጠ ተጠቃሚ ያደርጋል።

